Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ በአፍሪካ ኢኮኖሚያ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ የሚያስችል የድጋፍ ምክረ ሀሳብ ለቡድን 20 አባል ሀገራት አቀረበች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ 19) ለመከላከል እና በአፍሪካ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ የሚያስችል ባለ ሶስት ነጥብ የድጋፍ ምክረ ሀሳብ ለቡድን 20 አባል ሀገራት አቀረበች።

የኮሮናቫይረስ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል ያለው ምክረ ሀሳቡ፥ በተለይም በዓለም ደረጃ የወጪ ንግድ መጠን መቀነስ፣ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች መንገራገጭ እና የጉዞ እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ክፉኛ መጎዳት እንዲሁም ከኢትዮጵያ አንፃር ከሀገሪቱ የአገልግሎት ወጪ ንግድ ውስጥ ሁለት ሶስተኛውን ገቢ የሚያመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያጋጠመው የበረራ ኢንዱስትሪ መቀዛቀዝ በኢኮኖሚዋ ላይ ስጋትን ደቅኗል ብሏል።

አሁን በአፍሪካ ሀገራት ላይ የተደቀነው የኢኮኖሚ ስጋት ሀገራት በግላቸው በሚወስዱት እርምጃ እና በፖሊሲ ብቻ የሚቀረፍ አይደለም ያለው የኢትዮጵያ ምክረ ሀሳብ፥ ይህንን ለመቋቋምም የተቀናጀ ዓለም አቀፋዊ ምላሽ ያስፈልጋል ብሏል።

ኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚመጣውን ጫና ለመቀነስ ከአጋር ሀገራት ጋር እየሰራች መሆኑን ያመላከተው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ፥ ኢትዮጵያ የቡድን 20 አባል ሀገራት በቀጣይ በሚያደርጉት ልዩ ስብሰባቸው ከግምት ውስጥ ቢያስገቧቸው ያለችውን ባለ ሶስት ነጥብ ምክረ ሀሳብ ማቅረቧንም ገልጿል።

ከእነዚህም አንደኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የኮቪድ-19 የአስቸኳይ ጊዜ የፋይናንስ ድጋፍ ማዕቀፍ ሲሆን፥ በዚህም 150 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ እና የገንዘብ ድጋፉም የውጭ ምንዛሬ አቅምን እና የሴፍቲ ኔት መርሃ ግብሮችን ለማጠናከር የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

ሌላኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የአስቸኳይ ጊዜ የጤና ማዕቀፍ ሲሆን፥ በዚህም ለዓለም ጤና ድርጅት የሚደረገውን ድጋፍ በማጠናከር ድርጅቱ በአፍሪካ የሚያደርገውን ድጋፍ ማሳደግ፤ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል /ሲዲሲ/ እንዲሁም ለኤድስ፣ ወባ እና ቲቢ መከላከያ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ድጋፎችን ማጠናከር የሚለውም በምክረ ሀሳቡ ተካቷል።

ሶስተኛው በኢትዮጵያ የቀረበው ምክረ ሀሳብ በአፍሪካ ሀገራት ላይ ያሉ እዳዎች እንዲሰረዙ እና የብድር መመለሻ ጊዜዎች እንዲራዘሙ የሚጠይቅ ሲሆን፥ በዚህም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ላይ ያሉ የብድር ወለዶች እንዲሰረዙ እንዲሁም፤ የመክፈያ ጊዜያቸው የተቃረቡ ብድሮች ደግሞ ቢያንስ ለ10 ዓመታት ቢራዘሙ በሚል ጠይቃለች።

 

በሙለታ መንገሻ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.