Fana: At a Speed of Life!

በኢኮኖሚ አሻጥር ላይ በተሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የተጠናከረ ምርመራ እየተደረገ ነው – ፌዴራል ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና በሌሎች የኢኮኖሚ አሻጥሮች ላይ በተሳተፉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የተጠናከረ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

የኢኮኖሚ አሻጥር ኢኮኖሚን በማዳከም በሀገር እና መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ለመግዛት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት እና በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ሕገ-ወጥ ቡድኖች የሚፈጥሩት ሴራ ነው።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የታክቲክ ወንጀሎች ምርመራ ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ብርሀኑ አበበ÷የኢኮኖሚ አሻጥር ሕገ-ወጥ ቡድኖች በመንግሥት እና ሕዝብ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚጠቀሙበት ድምፅ አልባ ጦርነት መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ በኋላ በሕገ-ወጥ መንገድ መበልጸግ የሚፈልጉ ቡድኖች ግብር ለመሰወር በማሰብ አሊያም የሀገርን ኢኮኖሚ ለማዳከም በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እየተሳተፉ መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ከኅብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ እና በሚያከናውነው ጥልቅ ምርመራ አማካኝነት የውጭ ምንዛሬ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በማድረግ እና በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የተሳተፉ ግለሰቦች እና ድርጅቶችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ መጀመሩን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ባደረገው ምርምራ በሕጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የተሳተፉ 25 ግለሰቦች እና ድርጅቶች የሂሳብ አካውንት መታገዱን ገልጸዋል።

ፖሊስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በ25 ድርጅቶች እና ግለሰቦች ላይ ባደረገው ምርመራ በአጭር ጊዜ ውስጥ አምስት ቢሊየን 115 ሚሊየን 814 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ያለግብይት ማንቀሳቀሳቸውን እንደደረሰበት መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.