Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሸገርን ማስዋብ ምዕራፍ ሁለት መርቀው ከፈቱ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግንባታው የተጠናቀቀውን የሸገርን ማስዋብ ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት መርቀው ከፈቱ።

በምርቃ መርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የመዲናዋ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት አዲስ አበባ ንጹህና ለስሟ የሚመጥን ገጽታ እንዲኖራት በማድረግ ለዜጎች የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ታስቦ የተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የተጀመረና በቅርብ ክትትላቸው በጥራትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ማወቅ ተችሏል።

ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በሌላ ስፍራ ጸድቀው የነበሩ ከ4 ሺህ የሚበልጡ ሀገር በቀል ዛፎችን ወደዚህ ስፍራ ተዘዋውረው እንዲተከሉ ተደርጓል፡፡

ይህም መንግሥት በማንኛውም ሀገራዊ የልማት ሥራዎቹ ውስጥ ለአረንጓዴ ልማት ያለውን ተግባራዊ ቁርጠኝነት አመላካች እንደሆነም ነው የተነሳው፡፡

በተጨማሪም አንድ ከተማ እንደከተማ ማሟላት ያለባትን የአረንጓዴ ሥፍራ መስፈርት እንዲኖራት ለማድረግም አሁን ከተማዋ ያለችበትን እጅግ ዝቅተኛ የአረንጓዴ ሥፍራ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በመሠራት ላይ ላለው ሥራ የራሱን አስተዋጽዖ ያበረክታል ተብሎለታል።

የልጆች መጫወቻ ስፍራ ከ8 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናትና ታዳጊዎች የተሰሩና በተለያዩ ህብረ ቀለማት የተዋቡ የመጫወቻ ሥፍራዎችን በውስጡ አካቷል።

በሥፍራው ልጆች በምናባቸው ምስል የመከሰት ልምዳቸውን እንዲያዳብሩና አዕምሯቸውን ነፃ ለማድረግ የሚያስችላቸው የተፈጥሮን ድምጽ የሚያስተጋቡ የተለያዩ የድምጽ መሣሪያዎች ተገጥመውለታል።

ህጻናት ልዩ ልዩ የጨዋታ ዓይነቶች ለመጫወት የሚያስችለው ይህ ስፍራ ፥ ለልጆች የተዘጋጀ የተፈጥሮ ሳይንስ ማሳያ፣ የጤፍ ዓፅቅ፣ ባለብዙ ቀለማት የሩጫ ትራክ፣ ልዩ የስነ ምህዳር የአትክልት ስፍራ፣ የመረብ ኳስ መጫወቻ፣ የአዕዋፍ ዜማ ማድመጫ፣ የብስከሌት ማቆሚያ፣ የትንንሽ ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ፣ የጎብኚዎች ማዕከል፣ የግድግዳ ላይ ስዕል መሳያ፣ የአትክልት ቦታ ካፍቴሪያ እና የመሳሰሉትን አካቷል።

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ለሁሉም የዕድሜ ከፍሎች የተዘጋጀ ሲሆን ፥ እንደ ቅርጫት ኳስና እግር ኳስ ያሉ የስፖርት ዓይነቶችን ለመጫወትና የቡድን ልምምድ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡

ሌላኛው የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የሠርግ አጸድ ሲሆን ፥ በውስጡ የሙሽሮች ሰገነት፣ የአበባ ሰገነት፣ የሰርግ መናፈሻ አገልግሎት ማዕከል፣ የውሃ ምንጭ፣ የውሃ ዳር ሰገነትና የመሳሰሉትን አካቷል።

ይህም ተጨማሪ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን፣ የመመልከቻ ማማ፣ አነስተኛ የቅርጫት ኳስ መጫወቻ ስፍራዎች፣ 3 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተበከለ ፍሳሽን ማከም የሚችል ጣቢያና ከወንዙ ማዶ ያለውን የፓርኩን ሥፍራ የሚያገናኝ ድልድይ ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም ሥፍራው ለልደት እና ለመሳሰሉት ማኅበራዊ ዝግጅቶች ሊውል ይችላል።

1.2 ኪ.ሜ የወንዝ ዳርቻ ልማትን የያዘው ይህ ሥፍራ የፕሮጀከቱ አካል የወንዞችንና የወንዞች ዳርቻ ልማትን ጠቀሜታ አጉልቶ እንደሚያሳይ ተመላክቷል።

የወንዞች ዳርቻ ልማቱ የአፈር መሸርሸርን የሚከላከሉ ግድግዳዎች ሥራ፣ ወንዙን የማጽዳትና የውሃን መደበኛ ፍሰት ማስቀጠል የመሳሰሉ ሥራዎች ተሠርተውበታል።

የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት በአጠቃላይ በአንድ ጊዜ ከ325 በላይ መኪናዎችን ማቆም የሚያስችል ስፍራ አለው።

ፕሮጀክቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከ5oo ዜጎች በላይ ያሳተፈ ሲሆን ፥ በቋሚነት ለ3oo ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

በሐብታሙ ተ/ሥላሴ እና አፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.