Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረሃይል ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጭ የሆኑ ስብሰባዎች አይካሄዱም- ብልፅግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረሃይል ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጭ የሆኑ ስብሰባዎች እንደማይካሄዱ የብልፅግና ፓርቲ አስታውቋል።
 
የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አወሉ አብዲ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ ፓርቲው ያዘጋጀው የሶስተኛው ዙር የዝቅተኛ አመራር ስልጠና በቫይረሱ ምክንያት በሚፈለገው መጠን እየተካሄደ አለመሆኑን ገልፀዋል።
 
ስልጠናው በተጀመረባቸው አካባቢዎች የቫይረሱ መከላከል ብሄራዊ ግብረሃይል ባስቀመጠው አቅጣጫ ርቀት ጠብቆና የሰው ቁጥር ቀንሶ እንዲሁም ቀናቱን በማሳጠር እየተካሄደ መሆኑን ነው የገለጹት።
 
ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰፊ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ያሳተፉ ስብሰባዎች መካሄዳቸውን ያነሱት ሃለፊው፥ ይህ ሁኔታ ለቫይረሱ መስፋፋት የሚኖረውን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት የእርምት እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።
 
በሌላ በኩል ሁኔታውን ለራሳቸው የፓለቲካ ሃሳብ ሊጠቀሙበት የፈለጉ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል።
 
በስብሰባዎቹ አመራሩ ራሱን እና ቤተሰቡን ከቫይረሱ ለመጠበቅ የሚያስችለው ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።
 
ከዚህ በኋላ የሚካሄዱ ሁሉም ስብሰባዎች ብሄራዊ ግብረ ሃይሉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንደሚካሄዱ የገለጹት አቶ አወሉ፥ ከዚህ የወጡ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙም የእርምት እርምጃዎቸ ይወሰዳል ነው ያሉት።
 
ሰልጣኞቹ የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ እና ቫይረሱን መከላከል ላይ አተኩረው እንደሚወያዩ እና ሁሉም ስብሰባዎች በጤና ባለሙያዎች ቅርብ ክትትልና ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚካሄዱም ተናግረዋል።
 
ቫይረሱን በመከላከል ሂደት የብልፅግና ፓርቲ እንደመንግስትም ወሳኝ ሚናውን መወጣት ይቀጥላል ያሉት አቶ አወሉ፥ የዋጋ እና የዕቃ አቅርቦት ላይ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
 
በሃብታሙ ተክለስላሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.