Fana: At a Speed of Life!

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከ2 ተቋማት ጋር የሶስትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሁለት ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የሶስትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ሰነዱን የተፈራረመው የአሊባባ ቢዝነስ ግሩፕ አጋር ከሆነው ዌል ክላውድ ከተባለ የቴክኖሎጂ ተቋም እና ከሀገር በቀሉ ከሃሊ የስትራቴጂክ አማካሪ አገልግሎት ድርጅት ጋር ነው፡፡

ስምምነቱ ግዙፉን ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መገበያያ ቴክኖሎጂ በማቅረብ የሚታወቀውን የአሊባባ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥርዓት በኢትዮጵያ ለማስጀመር ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ቴክኖሎጂውን ዕውን ለማድረግ አስፈላጊ የሆነውን የዳታ ቋት እና ሌሎች ደህንነታቸው የተጠበቁ መሠረተ ልማቶችን እንደሚያቀርብ በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና÷ስምምነቱ ዓለም እየተጠቀመበት የሚገኘውን ቴክኖሎጂ ለሀገራችን በማስተዋወቅ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ዲጂታል የኢኮኖሚ ሽግግር እንደሚያፋጥን ተናግረዋል፡፡

የዌል ቴክኖሎጂ ግሩፕ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሽያጭ ዳይሬክተር ዢዬ ይ በበኩላቸው÷ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በቴክኖሎጂው ዘርፍ አብሮ ለመስራት በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የከሃሊ የስትራቴጅክ አማካሪ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤርሚያስ አመልጋ ÷ ሀገርን በመሰል የቴክኖሎጂ ዘርፎች ተጠቃሚ በማድረግ በብዙ መስኮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ የኢትዮጵያ ባንኮች እና የፋይናንስ ዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.