Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና ለመከላከል መንግስት ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆን አለባቸው – አቶ ደመቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሃገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና ለመከላከል መንግስት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳስበዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሄራዊ የአደጋ ስጋት መከላከል እና ምላሽ ሰጪ ግብረ ሃይል ከጤና ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በቅንጅት የመንግስትን ውሳኔዎች ተፈፃሚ እንዲያደርጉ እና እንዲከታተሉ ብሄራዊ ስምሪት መስጫ መድረክ ተካሄዷል።

ብሄራዊ ግብረ ሃይሉን እና የቴክኒክ ኮሚቴውን በበላይነት የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፥ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት እና ለመከላከል መንግስት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

በየደረጃው የመንግሥት ተቋማት ፍፁም በሰመረ ቅንጅት ለውሳኔዎቹ ተፈፃሚነት በልዩ ትኩረት እና ክብደት መረባረብ እንደሚጠበቅባቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

“በታሪካችን እጅግ የከፋ ፈተና ውስጥ መሆናችንን በውል በመገንዘብ፥ ሃገር እና ህዝብን በፍጥነት ለመታደግ ዳር እስከዳር ስትራቴጃዊ ርብርብ የምናደርግበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለንም” ብለዋል።

ብሄራዊ ርብርቡ በአጭር ጊዜ ትርጉም አዘል ውጤት ለማምጣት እንዲያስችል መንግሥት የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች በተሟላ መንገድ ተፈፃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ብሄራዊ ግብረ ሃይሉ እና የቴክኒክ ኮሚቴው ለተሰጠው ሃገራዊ ተልዕኮ ውጤታማነት ዕለት በዕለት ጥብቅ የአመራር ድጋፍ እና ጠንካራ ክትትል እንደሚደረግለት ተናግረዋል።

በሃገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና ለመከላከል መንግሥት በፌደራል ደረጃ የሚወስዳቸው እርምጃዎች በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ወጥነት ባለው አግባብ ተግባራዊ እንደሚደረጉም አስታውቀዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ መንግሥት ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ተፈፃሚነት እና ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ተግባራዊነት የተሟላ ውጤት ለማረጋገጥ ጥብቅ አመራር እንደሚጠይቅም አብራርተዋል።

ከዚህ ቀደም እንደሃገር ለገጠሙ አስቸጋሪ የተፈጥሮ አደጋዎች በመንግሥት የተሰጡት ስኬታማ ምላሾችን በማስታወስ፥ በሳል ልምዶች እና ውጤታማ ተሞክሮዎች በብሄራዊ ስምሪቱ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።

እንደሃገር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና ለመከላከል እያንዳንዱ ዜጋ የመፍትሔው አካል በመሆን ሰብዓዊ እና ሃገራዊ ግዴታውን በተግባር እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.