Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሽብር ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች የሕክምና ቁሳቁሶችን  ድጋፍ አደረገች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሶማሊያ የሽብር ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች የሚውሉ የሕክምና መሣሪያዎችንና መድኃኒቶችን ለሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አበርክቷል፡፡

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ የተመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በሶማሊያ በመገኘት ነው በሽብር ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች የሚውሉ የሕክም ቁሳቁሶችን ያስረከበው፡፡

አገልግሎቱ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሀን በላከው መግለጫ÷ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከመከላከያና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከጤና ሚኒስቴር የተውጣጡ የልዑካን ቡድን አባላት የአልሸባብ የሽብር ቡድን ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በሞቃዲሾ ተገኝተው ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ÷ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በደረሰው ጉዳት ማዘኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለሶማሊያ መንግሥትና  ሕዝብ እንዲሁም ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትንና ብርታትን ተመኝተዋል፡፡

ልዑኩ ያበረከተው ድጋፍ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በሽብር ጥቃቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ላጋጠማት ሶማሊያና ለሀገሪቱ ዜጎች ያላቸውን ወገንተኝነት ለመግለጽ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ የሽብር ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያርግ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ የሕክምና ቁሳቁሶች መለገሱንም አገልግሎቱ ገልጿል፡፡

ድጋፉን የሶማሊያ የጤና  ሚኒስትር ዶክተር አሊ ሐጂ አደም ተረክበዋል፡፡

ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይደገሙ ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ ጸጥታና ደኅንነት አካላት ጋር የምታደርገውን የትብብርና የአጋርነት ሥራ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ነው የተገለጸው፡፡

የአልሸባብ የሽብር ቡድን ቅዳሜ ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በፈጸመው ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች እንደተገደሉና 300 ሰዎች ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸውም ተጠቅሷል፡፡

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.