Fana: At a Speed of Life!

ድምጻዊ አሊ ቢራ ለሙያውና ለኢንዱስትሪው የራሱን አሻራ ያሳረፈ ባለሙያ ነው – ድምጻዊ መሀሙድ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የክብር ዶክተር ድምጻዊ አሊ ቢራ ለሙያውና ለኢንዱስትሪው የራሱን አሻራ ያሳረፈ በመላው ኢትዮጵያውን ልብ ውስጥ ህያው ፍቅሩን የተከለ የተከበረ ባለሙያ ነው ሲል ድምጻዊ መሀሙድ አሕመድ ገለጸ፡፡

የድምጻዊ አሊ ቢራ የሙያ አጋሮች እና ወዳጅ ዘመዶቹ በቢሾፍቱ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በመገኘት ሃዘናቸውን እየገለፁ ነው።

ድምጻዊ መሀሙድ አሕመድ፣ ሄለን በርሄ ፣ ብርሃኑ ተዘራን ጨምሮ በርካታ የሙያ አጋሮቹም በአርቲስቱ ቤት በመገኘት ሀዘናቸውን ገልፀዋል።

ከክብር ዘበኛ ጀምሮ አብረው ሲሰሩ በቅርበት እንደሚተዋወቁ ያስታወሰው ድምጻዊ መሀሙድ አሕመድ ፥ ለሰው የሚያዝነውና በፍቅር ከሁሉም ጋር የኖረው ድምጻዊ አሊ ቢራ ግላዊ ባህሪውም ጭምር ብዙዎች እንዲወዱት እንዳደረገው ገልጿል።

ለሙያ እና ሙያተኛ ከፍተኛ ክብር እንዳለው የገለፀችው ድምጻዊ ሄለን በርሄም ፥ ጀማሪውንም አንጋፋውንም እኩል የሚያበረታታ፣ ለሁላችንም አርዓያ የሆነ የተከበረ ባለሙያ ነበር ስትል ገልፃለች።

የሙያ አጋሮቹና ወዳጆቹ ለመላው ቤተሰቡ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሀብታሙ ተ/ስላሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.