Fana: At a Speed of Life!

ማዕከሉ አዲስ የስንዴና የጤፍ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች አስተዋወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የወረኢሉ የግብርና ምርምር ማዕከል በ27 ሄክታር ላይ የሰራቸውን በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች የዳቦ ስንዴና የጤፍ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች አስተዋውቋል፡፡

ማዕከሉ የዘር ብዜት ሥራዎችን በመስክ ጉብኝቱ ላይ ለተገኙ የኢትዮጰያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ኃላፊዎች፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች አስጎብኝቷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ችሎት ይርጋ ፥ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በአዳዲስ የምርምር ቴክኖሎጂዎች የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ በአጭር ጊዜ ሥራ መጀመሩንም ነው ያነሱት፡፡

ማዕከሉ የአርሶ አደሮችን የምርት ማነቆዎችና ሌሎች ችግሮች ለመለየት ብሎም የምርምር አጀንዳዎችን በመቅረፅ እንዲሁም ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የምርምር ማዕከል ግንባታና ሌሎች መሠረተ ልማቶችም በቅርቡ እንደሚጀመሩም ነው የገለጹት፡፡

የአካባቢው አርሶ አደሮችም ÷ በቀጣይ በምርምር ማዕከሉ የእንሰሳትና የተፈጥሮ ሐብት ቴክኖሎጂዎች ከሰብል ቴክኖሎጂዎች ጋር ተቀናጅተው እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

የወረዳው አስተዳደር አቶ ሰለሞን አይቼው በበኩላቸው ÷ የወረ ኢሉ ግብርና ምርምር ማዕከል በአጭር ጊዜ ተገንብቶ በፍጥነት ወደ ሥራ በመግባቱ ያላቸውን አድናቆትና ተስፋ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የወረኢሉ የግብርና ምርምር ማዕከል በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥር 23ተኛ የምርምር ማዕከል ሆኖ ነው በግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን የተቋቋመው፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.