Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት የዜጎችን ዘላቂ ሰላም በማስጠበቅ በጋራ ለመበልጸግ የሚያስችል መሰረት የጣለ መሆኑን አስታውቋል።
 
ክልሉ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት የዜጎችን ዘላቂ ሰላም በማስጠበቅ በጋራ ለመበልጸግ የሚያስችለንን መሰረት የጣለ ነው።
 
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሰላም ስምምነቱ የታለመለትን ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።
 
የክልሉ መንግስት ቅድመ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ክልልና በአማራ ክልል ህዝብ መካከል ለክፍለ-ዘመናት የዘለቀው የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ባህላዊና መንፈሳዊ ትስስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለሰላም እጁን ዘርግቶ ሲጠባበቅ መኖሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
 
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት ለሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች ዳግም ትንሳኤ ወሳኝ ከመሆኑም በላይ ከቂምና ከቁርሾ የዘለለ ህብረትን፣ አንድነትንና የጋራ እሴትን በጋራ የምንገነባበትን መሰረት ይጥላል ብለን እናምናለን።
 
የደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት እውን መሆን እንደ ክልል መንግስት የምንፈልገውና አጥብቀን ስንመኘው የነበረ መሆኑን እየገለጽን ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን አበክረን እንገልፃለን።
 
ስለሆነም በጦርነቱ ምክንያት የወደመውን የሕዝብ ሀብት መልሶ ለመተካትና የዘላቂ መልሶ ግንባታ ሥራው እንዲፋጠን ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ እንደ ሕዝብ የተፈጠረውን የሰላም አየር ተጠቅመን መረባረብ ይኖርብናል።
 
ሰላም ወዳድ የሆነው ሕዝባችን የሰላም ስምምነቱ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ከደረሰብን ጉዳት ለማገገምና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት እንደወትሮው ሁሉ ከክልሉ መንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
 
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
 
ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም
 
ባሕር ዳር
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.