Fana: At a Speed of Life!

የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ላይ ትኩረት ይደረጋል – አቶ ርስቱ ይርዳ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ላይ ትኩረት ይደረጋል ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይረዳ ገለጹ።

በደቡብ ክልል የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ እየተካሔደ ነው።

ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ÷ በክልሉ ካለፉት ዓመታት በላቀ ደረጃ ስንዴ በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ በማልማት በዘርፉ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከስንዴ ባሻገር በጤፍ እና በቆሎ መሠረታዊ ሰብሎች ላይ ትኩረት በማድረግ አርሶ አደሩን በመደገፍ የተሻለ ምርት ለማግኘት በቁርጠኝነት መከናወኑን ነው የገለጹት፡፡

በሩብ ዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከፍተኛ ሕዝብ የተሳተፈበት የልማት ስራ ተሰርቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷በእንስሳት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በመኖ ልማት ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።

በቀጣይም በበጋ መስኖ እና በበልግ አዝመራ  ላይ ርብርብ በማድረግ ለምርትና ምርታማነት እድገት ይሠራል ነው ያሉት ፡፡

በግብርናው ላይ የተሻለ ውጤት የተመዘገበ ቢሆንም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በኩታ ገጠም ዘዴ የማልማቱ ሂደት በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን መጠቆማቸውንም  የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.