Fana: At a Speed of Life!

አንጋፋው የጥበብ ሰው አርቲስት ዓሊ ቢራ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አርቲስት ዓሊ ቢራ በሥራዎቹ የኦሮሞ ሙዚቃ በሀገሪቱ የሙዚቃ ገበያ ውስጥ ተገቢውን ሥፍራ እንዲያገኝ አስችሏል።

በልጅነቱ ያደረበትን የሙዚቃ ፍላጐት ለመኖር በ1954 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ በተለምዶ አፍረን ቀሎ ባንድ የሚባለው ኡርጂ በከልቻ ባንድ መቋቋም ለዓሊ ልዩ አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡

በወቅቱ የኡርጂ በከልቻ ባንድ በሥሩ ህሪያ ጃለላ የተባለ የታዳጊ አርቲስቶች የሙዚቃ ቡድን ስለነበረው ለዓሊ መሐመድ ሙሣ ህሪያ ጃለላ (የፍቅር ጓዳኞች) ባንድ አባል በመሆን የ60 ዓመታት የሙዚቃ ጉዞውን ጀመረ፡፡

የያኔው ዓሊ መሐመድ ሙሣ (አርቲስት ዓሊ ቢራ) በሕይወት በቆየባቸው ዘመናት 267 ዘፈኖችን ለአድማጭ አድርሷል፡፡

ዓሊ ከሚናገራቸው ሰባት ቋንቋዎች በሥድስቱ ማለትም÷ በአፋን ኦሮሞ፣ በሶማልኛ፣ በሐረሪ፣ በአማርኛ፣ በአረብኛ እና በስዊዲሽ ቋንቋዎች ዘፍኗል፡፡

የሙዚቃ ሥራዎቹን አሳትሞ ለአድማጭ በማድረስ የኦሮሞ ሙዚቃ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ገበያ ውስጥ ተገቢ ሥፍራ እንዲያገኝ ማስቻሉም ይነገርለታል፡፡

ዓሊ ስመ ብዙ ነው፤ በልጅነቱ ዓሊ መሐመድ ሙሣ እንዲሁም ብዙዎች እንደሚያውቁት በጥበብ ስሙ ዓሊ ቢራ ፤ በቅርብ ወዳጀቹ ደግሞ “Adeeroo” (አጎት) በሚል የፍቅርና የክብር ስም ይጠራ ነበር፡፡

የዋናው የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን ኡርጂ በከልቻ ባንድ በአንድ ወቅት ባሰናዳው የበዓል ዝግጅት ላይ ዓሊ ቢራ በ13 ዓመቱ “Birraadhaa barihee ililliin urgooftee” የተሰኘ የመጀመሪያ ዘፈኑን ለሕዝብ በማቅረብ ድምጻዊነቱን አስመሰክሯል፡፡
አርቲስት ዓሊ በሥራዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላቸው ከ100 በላይ ሸልማቶችን አግኝቷል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የላቀ አገልግሎት ላበረከቱ የሕዝብ ባለውለታዎች የሚሰጠውን ታላቅ የክብር ኒሻንን ተሸልሟል፡፡

ዓሊ ቢራ በስሙ÷ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ትምህርት ቤት፣ በአዳማ ከተማ ውስጥ መንገድ፣ በድሬዳዋ ከተማ ፓርክ ተሰይሞለታል።

ከተለያዩ የጥበብ ሽልማት አዘጋጅ ድርጅቶችም የዕድሜ ልክ የላቀ አገልግሎት ሽልማቶችን ተቀብሏል።

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሙዚቃ ትምህርት በመከታተል የጥበብ ዕውቀትና ክህሎቱን አሳድጓል፡፡

አርቲስት ዓሊ ቢራ ከድምጻዊነቱ ባሻገር የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች እንደሚጫዎት ይነገርለታል፡፡

ለአብነትም÷ ሊድና ቤዝ ጊታር፣ ፒያኖ፣ ኦርጋን፣ አኮርዲዮን፣ ኡድ እና የመሳስሉትን የሙዚቃ መሣሪያዎችን አሳልጦ ይጫወትየነበረ ሲሆን፥ የዜማ ደራሲ እና የሙዚቃ አቀናባሪም ነበር፡፡

ባለፉት 60 ዓመታት ለሙያው ታምኖ የኖረው ዓሊ÷ ከድሬዳዋ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል፡፡

ዓሊ ቢራ ከአባቱ አቶ መሐመድ ሙሣ እና ከእናቱ ወይዘሮ ፋጡማ ዓሊ በ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ገንደ ቆሬ እንደተወለደ የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡

አርቲስት ዓሊ ቢራ ከወ/ሮ ሊሊ ማርቆስ ጋር ትዳር መስርቶ ይኖር ነበር፡፡

ባጋጠመው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በተወለደ በ75 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ ስታዲየም የሽኝት መርሐ ግብር ከተካሄደ በኋላ የቀብር ሥነ ስርዓቱ በለገሀሬ የሙስሊም መካነ መቃብር ይፈጸማል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.