Fana: At a Speed of Life!

“ዓለም ወደ ገሃነምነት እየተለወጠች ነው” – አንቶኒዮ ጉተሬዝ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ትናንት በግብፅ ሻርም ኤል ሸክ እየተካሄደ በሚገኘው 27ኛው የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ መድረክ ላይ ዓለም ወደ ገሃነምነት እየተቀየረች ነው ሲሉ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተናገሩ፡፡

የዓየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አደጋ በተመለከተ ዓለም ከወዲሁ የካርበን ልቀት መጠንን የመቀነስ ወይም የዓየር ንብረት ለውጥ ለሚያስከትለው ጥፋት መጪውን ትውልድ የመውቀስ ሁለት አማራጮች አሏት ሲሉም ነው ያስጠነቀቁት፡፡

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የዓየር ንብረት ለውጥን እንዴት መግታት እንደሚቻል ለመምከር ከሀገራት ለታደሙት ልዑካንም “የሰው ልጅ ምርጫ አለው ፤ የዓየር ንብረት ለውጥን ለመግታት በትብብር መሥራት ወይም መጥፋት” ሲሉም ነው የተደመጡት፡፡

ጉባዔው ከዓየር ንብረት ለውጥ እና እንዴት መግታት እንደሚቻል ከመምከር በተጨማሪ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ግጭት እና እየጨመረ ባለው ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት እንዲሁም የኃይል አቅርቦት እጥረት ላይም መክሯል ነው የተባለው፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊ አያይዘውም በካይ ጋዝ ከሚያመነጩ የኃይል አማራጮች ወደ አረንጓዴ የኃይል አማራጭ የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን የዓለማችን በኢኮኖሚ የበለጸጉ ሀገራት እና ታዳጊ ሀገራት ጥምረት መመሥረት አለባቸውም ብለዋል፡፡

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ÷ ሽግግሩን ለማሳለጥ እና ጥምረቱ ዕውን እንዲሆን በተለይ ቻይና እና አሜሪካ ልዩ ኃላፊነት አለባቸውም ነው ያሉት።

ከአንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቀጥሎ የቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት አልጎር የተናገሩ ሲሆን ÷ እርሳቸውም ዓለማችን በካይ የኃይል አማራጭ ላይ ያላት ጥገኝነት ማክተም አለበት ብለዋል፡፡

በተለይ የዓየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ላይ የሚያደርሰው ቀውስ ዕልባት ማግኘት አለበትም ነው ያሉት፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.