Fana: At a Speed of Life!

የግብርናው ዘርፍ በሚፈለገው ደረጃ አድጎ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ  ድጋፋችንን እንቀጥላለን- ፋኦ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል የግብርናው ዘርፍ በሚፈለገው ደረጃ አድጎ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ገለጸ፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  ርስቱ ይርዳ ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካይ  ፋራይ ዚሙድዚ ጋር ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ የአርሶ አደሩን ገቢና የአመጋገብ ስርዓት ለማሻሻል ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን አቶ ርስቱ አስረድተዋል፡፡

ዘርፉ ሕዝቡን በአግባቡ ከመመገብ ባለፈ የሀገሪቱ የዕድገት መሰረት እንዲሆን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በተለይም በቅርብ የተጀመረው በእያንዳንዱ አርሶ አደር ደረጃ የአመጋገብ ስርዓትና ምጣኔ ለማሻሻል እየተተገበረ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ተስፋ ሰጭ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

እንደ ፋኦ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘርፉን በማዘመን፣ በግብይት ስርአት፣ በማሽነሪ አቅርቦትና በአቅም ግንባታ  ረገድ ድጋፍ እንዲያደርጉ አቶ ርስቱ ጠይቀዋል፡፡

ፋራይ ዚሙድዚ  በበኩላቸው÷ ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስምንት የምስራቃዊ አፍሪካ ሀገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ በደቡብ ክልል የግብርናው ዘርፍ በሚፈለገው ደረጃ አድጎ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.