Fana: At a Speed of Life!

ለሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ለማድረግ አጋርነቱን እያሳየ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለሰላም ስምምነቱ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለሰ አለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ÷ ኢትዮጵያ ጉዳዩ አፍሪካዊ መፍትሔ ያግኝ ብላ የጸና አቋም መያዟ ጉልህ ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ  አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል እና የሃሳብና ጥበብ እጥረት እንደሌለባት ያሳየችበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የተለያዩ  ሀገራት እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት  መንግስት እና ህወሓት ግጭት ለማቆም የደረሱበትን ስምምነት በአዎንታ እንደሚቀበሉትና ድጋፍ እንደሚያደርጉ መልዕክቶች ማስተላለፋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የህወሓት ታጣቂዎች አዛዦች በስምምነቱ መሰረት ኬንያ ናይሮቢ መገናኘታቸው በጎ ጅምር ተደርጎ እንደሚወሰድም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወዳጆች እና አጋሮች በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ዳግም ለመገንባትና የተፈናቀሉትን ለማቋቋም እንዲሁም የህወሓት ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት እንደግፋለን ማለታቸውንም አንስተዋል፡፡

ከዚህ ችግር ለመውጣት ከሀገር ውስጥም  ሆነ ከውጭ  የሚኖር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሰላም በመቆም ስምምቱን መደገፍ እና ተጎጂ ወገኖቹን መርዳት ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡

ዳያስፖራው እንደ ሰላም አርበኝነቱ የወገኖቹ እንባ እንዲታበስ፣ የተፈናቀሉት እንዲቋቋሙና የፈረሰው እንዲጠገን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአዲሱ ሙሉነህ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.