Fana: At a Speed of Life!

ከተማ አስተዳደሩ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን አበረከቷል፡፡

የአካባቢው አርሶ አደሮችም ከተማ አስተዳደሩ በማቆያ እንዲገቡ ላደረጋቸው አቅመ ደካማዎች የሚውል የሰብል ምርቶች በስጦታነት አበርክተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባ ኢንጅበር ታከለ ኡማ ለአርሶ አደሮቹ የተበረከቱትን የንጽህና ማጠበቂያ ቁሳቁሶች አስረክበዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው ጊዜው ከምንም ጊዜው በላይ መደጋገፍንና ወንድማማችነትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ ያደረጉት የሰብል ድጋፍም መደጋገፍን በተግባር ያሳየ እንዲሁም ለብዙዎች ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

ኢንጅነር ታከለ የተለያዩ መሰረታዊ ፍላጎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች “ተግባራችሁ ህገወጥ ብቻ ሳይሆን ልኩን ያለፈ ኢሰብአዊነት ነው፡፡እንዲህ አይነት ተግባር ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ጉዳይ በተለየ መልኩ በከፍተኛ የህግ ጥሰት የሚታይ ነው” ብለዋል፡፡

ህገወጥ ተግባራት እንዲቀጥሉ የከተማ አስተዳደሩ አይፈቅድም ያሉት ምክትል ከንቲባው የተጠናከረ እርምጃም ይወስዳል ማለታቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተለያየ የጥበብ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አርቲስቶች በርክክቡ ወቅት ተገኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.