Fana: At a Speed of Life!

ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የዓሊ ከተማ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓሊ ከተማ የዋቤ ድልድይ ኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

56 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአስፋልት መንገድ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ከመንገዶች ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ግንባታው በ2 ቢሊየን 153 ሚሊየን 60 ሺህ 671 ብር ወጪ የቻይናው ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ የተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

የግንባታው ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን፥ ፕሮጀክቱ የአራት ድልድዮች ግንባታና ከባድ የቆረጣ ሥራዎች የተከናወኑበት እንደነበረም ተነግሯል፡፡

የፕሮጀክቱ ዕውን መሆን በአካባቢው በሥፋት የሚመረቱትን የስንዴ፣ ገብስ እና የፍራፍሬ ምርቶችን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ምርቶችን በሥፋት እና በጥራት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገልጿል፡፡

መንገዱ በዋናነት ሮቤ፣ ዓሊ እና ዋቤ ከተሞችን በቅርበት በማገናኘት የቱሪዝም መዳረሻ የሆኑትን የሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የሳነቴ አምባ እና የዲንሾ ብሔራዊ ፓርክ ለጎብኝዎች ምቹ ያደርጋልም ነው የተባለው፡፡

የፕሮጀክቱ ቀጣይ ምዕራፍ የሆነው የዋቤ ወንዝ – አርሲ ሮቤ ክፍል-2 የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት በግንባታ ላይ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁም ፥ ከአዲስ አበባ ባሌ ሮቤ ለመጓዝ ይወስድ የነበረውን የጉዞ ርቀት በ100 ኪሎ ሜትር ያሳጥረዋል ተብሏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.