Fana: At a Speed of Life!

በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ ከ140 ሺህ በላይ ወገኖች ወደቀያቸው መመለስ ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ ከ140 ሺህ በላይ ወገኖች ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለስ መጀመራቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን አስታወቀ።

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው÷ በዞኑ ከተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን ወደቀያቸው መመለስ ጀምረዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ ተፈናቅለው የቆዩ ከ140 ሺህ በላይ ወገኖችን የደባርቅ ከተማ ማኅበረሰብ፣ ባለሐብቶች፣ታዋቂ ግለሰቦችና ድርጅቶች ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል ተብሏል።

አሁን ላይ አካባቢው ወደ ሰላም በመመለሱ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ተፈናቅለው የቆዩ ወገኖችን ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆናቸውን የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት ገልጸዋል፡፡

ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ የሚገኙ ወገኖች ለረጅም ጊዜ ተፈናቅለው የቆዩ ከመሆኑ ባለፈ ሐብት ንብረታቸውን ያጡና ቤት የወደመባቸው ስለሆነ ጠንካራ መልሶ የማቋቋም ሥራ ይጠይቃል ተብሏል።

መልሶ የማቀቋም ሥራውን ለማከናወንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እቅድ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት ሃላፊው።

የተጎዳውን ማኅበረሰብ መልሶ የማቋቋም ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ለወገን ተቆርቋሪ ነን፤ ሰብዓዊነት ጉዳያችን ነው የሚሉ አካላት በሙሉ ፊታቸውን ወደ ሰሜን ጎንደር ዞን እንዲያዞሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ተመላሾቹ ከተፈናቀሉበት ጊዜ ጀምሮ ከጎናቸው ለነበሩት የደባርቅ ከተማ ማኅበረሰብ፣ ለረጅ ድርጅቶች፣ ለተቋማትና ሌሎች አካላት ምሥጋና ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.