Fana: At a Speed of Life!

በሶማሊያ የመረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ኃላፊ የተመራ ልዑክ በኢመደአ ጉብኝት አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በሶማሊያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ የተመራ ልዑክ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ጎበኘ፡፡

ከፍተኛ ልዑኩ በኢመደአ በነበረው ጉብኝት የኢንፎርሜሽን እና ኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማት ደህንነት በማረጋገጥ በኩል በአስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉ የቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ሥራዎችን እንዲሁም የኢትዮ ሳይበር ታለንት ልማት ማዕከልን ተመልክቷል፡፡

ልዑካን ቡድኑ ኢመደአ ከውጭ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት በመላቀቅ ሃገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን በማረጋገጥ በኩል ሰፋፊ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ በቀጣይም ቀጠናዊ የሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታው ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚደረጉ የመረጃ ልውውጦች፣ በአቅም ግንባታ መስኮች እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በሚደረጉ የጋራ ስምሪቶች ዙሪያ የተለያዩ ምክክሮችን እንደሚያደርግም ከኢመደአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሶማሊያ የመረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ከፍተኛ የልዑክ ቡድን ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት በትላንትናው እለት አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.