Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ አሳይታለች፡፡

ኢትዮጵያ በግብፅ ሻርማል ሼክ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ ያላትን ተሞክሮ አካፍላለች፡፡

በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የዓለም አቀፍ የአካባቢ ስምምነቶች ድርድር ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ መንሱር ደሴ በመድረኩ ባቀረቡት ሪፖርት ÷ባለፉት 50 ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስረድተዋል፡፡

በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጽዕኖው እየጨመረ መምጣቱን እና እንደ ጎርፍ፣ ድርቅና ሌሎች ተፈጥሯዊ ክስተቶች በሀገሪቱ  በተደጋጋሚ እየተከሰቱ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተፈተነች መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ÷በሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አንስተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት 8 ነጥብ 1 ሚሊየን ሰዎች ከድርቁ ጋር በተያያዝ ለጉዳት ሲዳረጉ  ከ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ የቀንድ ከብቶች ደግሞ ለሞት መዳረጋቸውን በሪፖረቱ ጠቁመዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ብሄራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ማጣጣሚያ ፕላን በማዘጋጅት የተከሰተውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ጥረት እያደረገች መሆኑንም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግስት እየተተገበረ ያለውን ዘላቂ የመሬት አያያዝ ስርዓትና በበጋው ወቅት በዜጎች ተሳትፎ የሚተገበረው የተፋሰስ ልማት ስራ ዓለም ትምህርት ሊወስድበት የሚገባ  መልካም ተሞክሮ ሆኖ በመድረኩ ቀርቧል፡፡

መንግስት ችግሩን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎችን ቢሰራም የፋይናንስ እጥረት እና የበለፀጉ ሀገራትና የልማት አጋሮች ድጋፍ ማነስ በጥረቱ ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነ መጠቀሱንም  ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.