Fana: At a Speed of Life!

ሕብረት ባንክ “ሕብር ኢ-ኮሜርስ” የተሰኘ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ አገልግሎት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕብረት ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር “ሕብር ኢ-ኮሜርስ” የተሰኘ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ አገልግሎት ይፋ አድርጓል፡፡
 
በማስተር ካርድ የክፍያ ጌትዌይ የሚሰራው “ሕብር ኢ-ኮሜርስ” በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ኦንላይን ለዓለም አቀፍ ደንበኞች እንዲሸጡና አዳዲስ ደንበኞችንም እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል፡፡
 
“ሕብር ኢ-ኮሜርስ” በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ ተቋማትና ነጋዴዎች በማስተር ካርድና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ካርዶች ክፍያ ከኢትዮጵያ ውጭ ካሉ ደንበኞች መቀበል እንዲችሉ የሚረዳ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
 
ስርዓቱ የሀገር ውስጥ ንግዶች አዳዲስ ዓለም አቀፍ ገበያዎችን ማግኘት እንዲችሉና ገቢያቸው እንዲያድግ ብሎም ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚው ገበያ እንዲኖራት የሚያግዝ መሆኑም ተገልጿል፡፡
 
“ሕብር ኢ-ኮሜርስ” ሻጮች ለሸጡት ምርት ክፍያቸውን በውጭ ምንዛሬ ያለምንም እንግልትና መዘግየት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን÷ የክፍያ ስርዓቱ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲያድግም አስተዋፅኦ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡
 
የሕብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ከበደ÷ የሕብር ኢ-ኮሜርስ ተግባራዊነት ከባንኩ ስትራቴጂ 2030 ጋር የሚጣጣምና በዓለም አቀፍ የክፍያ ስርዓት ውስጥ በካርድ ባንኪንግ ለሚገበያየው ደንበኛ እና ለነጋዴው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡
 
የማስተር ካርድ የምስራቅ አፍሪካ ካንትሪ ማኔጀር ሺኸርየር ዓሊ በበኩላቸው ÷“ሕብር ኢ-ኮሜርስ” ነጋዴዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የኦንላይን የክፍያ ጌትዌይ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችላቸውና ክፍያቸውን መቀበል፣ የደንበኞቻቸውን ቁጥርና ገቢያቸውን ማሳደግ እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል፡፡
 
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.