Fana: At a Speed of Life!

የጤና ባለሙያዎችን በጥናት በተደገፉ አሰራሮች ማገዝ ለዘርፉ ውጤታማነት ፋይዳው የጎላ ነው-ዶ/ር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ሕዳ ር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጥናት የተደገፉ አሰራሮችን በመዘርጋት ለጤና ባለሙያዎች ድጋፍ ማድረግ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው ሲሉ የጤና ሚኒስተር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

የጤናው ዘርፍ የሰው ሃብት ልማት፣ ብቃትና አስተዳደርን በጥናት በተደገፈ መልኩ ለማሻሻል የሚያስችል የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል ፡፡

ዶክተር ሊያ ÷በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ የጤና ባለሙያዎችን በጥናት በተደገፉ አሰራሮች መደገፍ ለጤና ሽፋኑ መሳካትና ለአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገቱ መፋጠን ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት በተለያዩ ወረርሽኞች ምክንያት በዘርፉ ሙያተኞች ላይ የተፈጠረውን ጫና ከባድ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ለዚህም በአገልግሎት ላይ የተሰማሩ የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ተሰላፊ ሆነው የሚገጥማቸውን ፍልሚያ በተለያዩ ድጋፎች ማገዝና በጥናት የተደገፉ አሰራሮችን በመዘርጋት ማበረታታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮኔ በበኩላቸው÷ የዓለም ባንክ የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎችን ለመደገፍ ለሚሰራው ስራ በቴክኒክና በፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.