Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም  ወንጀሎችን ከሚፈፅሙ ግለሰቦች ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ስልክ እየደወሉ እና የተለያዩ የማጭበርበር ዘዴዎችን በመጠቀም ወንጀሎችን ከሚፈፅሙ ግለሰቦች ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪ አቀረበ ፡፡

በአዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ስልኮች በመደወል እንኳን ደስ አላችሁ ሎተሪ ደርሷችኋል ፣ሲስተም እያስተካከልን ነው፣ የሞባይሎትን አቅም ከ4ጂ ወደ 5ጂ እየቀየርን ነው በማለት ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ከሌሎች ባንኮች ጋር ኦንላይን ሲስተም እየጀመርን  ነው በሚሉ እና ሌሎች ማደናገሪያዎችን በመጠቀም የተለያዩ ግለሰቦች የማጭበርበር ወንጀል እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ መረጋገጡ ተጠቁሟል፡፡

አንዳንዶቹም የማጭበርበሪያ ስልቶች ደግሞ ደዋዮቹ ግለሰቦች እንዲያምኑ በኤቲም ገንዘብ ያወጡበት ትክክለኛ ቀን በመናገር  የወንጀሉ ሰለባ እያደረጓቸው መሆኑን ነው  የተገለጸው፡፡

ይህን ተከትሎም  የግለሰቦች የባንክ ሚስጢር የሚወጣበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ፖሊስ አስታውቋል።

ወንጀሉ በልዩ ልዩ የአፈጻጸም ስልቶች እየተፈፀመ ከመሆኑም ባሻገር ስልክ በመንጠቅና ቴክኒካል የሆኑ ዘዴዎችን በመጠቀም የግለሰቦችን የባንክ አካውንት ወደ ቴሌ ብር በማስተላለፍ ወንጀሉ እየተፈጸመ ይገኛል ተብሏል፡፡

ፖሊስ አያይዞ እንደጠቀሰው ወንጀሉን ለመከላከል ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል የተለያዩ የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች ቢተላለፉም አሁንም ወንጀሉ እየተፈጸመ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ግለሰቦች የማያውቋቸው የስልክ ጥሪዎች እና የጽሁፍ መልዕክቶች ሲደርሷቸው ተገቢውን ማጣራት ማድረግ እንደሚገባቸው እና ጥሪው እንደደረሳቸው ወደ ተግባር ከመግባታው በፊት አቅራቢያቸው ወደሚገኝ ባንክ በመሔድ እውነታውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ፖሊስ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ፖሊስ መሰል ወንጀሎችን ለመቆጣጠር ከሚሰራው ሥራ ባሻገር አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ መረጃውን ለፀጥታ አካላት በመስጠት ህብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆንም ጥሪ መቅረቡን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.