Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና የሶማሊያ የመረጃና ደህንነት ተቋማት የአልሸባብን የሽብር ጥቃት በጋራ ለመከላከል ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና የሶማሊያ የመረጃና ደህንነት ተቋማት የአፍሪካ ቀንድ ስጋት የሆነውን አልሻባብን ለመከላከልና የሽብር እንቅስቃሴውን ለመግታት የሚያስችል የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥና የጋራ ዘመቻ ማካሄድ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

የመግባቢያ ሰነዱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና የሶማሊያ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ መፈራረማቸውን የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በስምምነቱ ወቅት፥ አልሸባብ በቅርቡ በሞቃዲሾ ከተማ በፈፀመው የሽብር ጥቃት እጅግ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ለኢትዮጵያና ሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድም የስጋት ምንጭ በመሆኑ ተቋማቸው የሽብር ቡድኑን የግንኙነት መረብ ሲያጠና መቆየቱን ጠቅሰዋል።

አሁንም በቡድኑ አባላት ላይ ጥብቅ ክትትል እያደረገ በመሆኑ ከሶማሊያ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ጋር የመረጃ ልውውጦችን በማድረግ በተመረጡ ቦታዎች በዘመቻ ስራዎች በመሳተፍ እንደሚያግዝና ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

የሶማሊያ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ በበኩላቸው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ከሶማሊያም አልፎ በአካባቢው ሃገራት ጭምር ድንበር ተሻግሮ ጥቃት በመሰንዘር ለአፍሪካ ቀንድ የሚፈጥረው ስጋት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ቡድኑ በአካባቢው የሚፈጥረውን ስጋት ለማስቀረት በሶማሊያና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኑን መሪዎችና ሴሎችን በጋራ በማጽዳት በኩል የኢትዮጵያና የሶማሊያ አቻ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን የመከላከልና የማምከን ከፍተኛ አቅምና ልምድ እንዳላትም ነው የገለጹት።

ከዚህ አኳያም የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ ለመግታት በመረጃ ልውውጥ፣ የተቀናጀ ፀረ አልሸባብ ዘመቻ ስምሪት በመውሰድና ቀጠናዊ ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ በኩል የተደረሰውን የትብብር ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ ውጤት እንደሚመዘገብ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

አልሸባብ ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ በመግባት በመለመላቸው ፣ ባደራጃቸውና ስምሪት በሰጣቸው አባላቱ ጥቃት ከፍቶ በተሰነዘረበት የአፀፋ ምት ከፍተኛ ኪሳራ መከናነቡ ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.