Fana: At a Speed of Life!

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል – የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።

በ2014/15 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን 400 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው በ2014/2015 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን ከ13 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት 400 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው።

በሀገሪቱ በቆላማ፣ ሞቃታማና መካከለኛ ቦታዎች ላይ ሰብል እየተሰበሰበ እንደሚገኝ እና በደጋማው አካባቢ ሰብል በመድረሰ ላይ እንዳለ ጠቁመዋል።

በተያዘው የመኸር ወቅትም ከማሳ ዝግጅት እስከ ሰብል አሰባሰብ ባሉት ወራቶች ምርታማነትን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

የግብርና ሚኒስቴርም የምርት ብክነትን ለመቀነስ ጤፍ፣ አኩሪ አተር፣ ስንዴን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከ1 ሺህ 500 በላይ ኮምባይነሮችን በማሰማራት ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስትቲዩት ትንበያ እንደሚያመለክተው በሚቀጥሉ ቀናት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊቀጥል ይችላል።

በመሆኑም በደረሰ ምርት ላይ ዝናብ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ፣ የግብርና ባለሙያው እና በየደረጃው የሚገኝው አመራር በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተያዘው የመኸር ወቅት ስንዴ አሰባሰብ ላይም የህብረት ስራ ማህበራትን ጨምሮ ተማሪዎች፣ የግብርና ሙያተኞችና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ በማድረግ በዘመቻ የሰብልን ብክነት ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.