Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ 10 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ ከሕዳር 11 እስከ 20 ቀን 2022 በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ የሰሜን፣ የሰሜን ምሥራቅ፣ የምሥራቅ፣ የመካከለኛው እና የደቡብ ደጋማ ቦታዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ይዘወተራል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም አንዳንድ የደቡብ ምዕራብ እና የምዕራብ እንዲሁም በጥቂት የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡

በመጭዎቹ 10 ቀናት ከኦሮሚያ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ቡኖ በደሌ፣ ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ የባሌና የአርሲ ዞኖች፣ ጥቂት የጉጂ፣ የቦረና የምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል፡፡

በተጨማም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና የሲዳማ ክልል አብዛኛው ዞኖች፣ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደግሞ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የጌዴኦ፣ የወላይታ እንዲሁም  የደቡብ ኦሞ እና የሰገን ሕዝቦች፣ ከአማራ ክልል የምዕራብ ጎጃምና የአዊ፣ የምዕራብ፣ የመካከለኛውና የሰሜን ጎንደር ዞኖች በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል።

የጋምቤላና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዞኖች እንዲሁም ድሬዳዋና ሐረሪ፣ ከሶማሌ ክልል የዳዋ፣ የሊበን፣ የቆራሄ፣ አፍዴር፣ የዶሎ እና የፋፈን ዞኖች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙም ነው የተገለጸው።

የመካከለኛው፣ የሰሜን ምሥራቅ እንዲሁም የአፋር አጎራባች ሥፍራዎች አልፎ አልፎ ከሚኖራቸው የደመና ሽፋን ለጥቂት ቀናት ቀላል ዝናብ የሚያገኙ ቢሆንም÷ ከመደበኛው ያነሰ ዝናብ አመዝኖባቸው ይቆያሉ ነው የተባለው።

የተቀሩት የሀገሪቱ ሥፍራዎች ደረቅ የአየር ሁኔታ አመዝኖባቸው እንደሚቆይ ከሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.