Fana: At a Speed of Life!

11 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በተባሉ ግለሰቦች፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ደላሎች ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ፖሊስ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የልማት ተነሺ ነን በማለት ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት 11 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በተባሉ ዘጠኝ ግለሰቦች፣ ወንጀሉ እንዲፈፀም ሁኔታዎችን አመቻችተዋል በተባሉ ሦስት የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና በ3 ደላሎች ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ዳትሰን ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የልማት ተነሺ ሳይሆኑ የልማት ተነሺ እንደሆኑ የሚያስመስል ሀሰተኛ ሠነድ በማዘጋጀት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል መባሉን የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

በተዘጋጀው ሀሰተኛ ሠነድ መሠረት በቀድሞ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ኮዬ ፈጬ ዘጠኝ እና በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ሁለት በአጠቃለይ 11 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ወስደዋል ብሏል ፖሊስ፡፡

ስለሆነም ዘጠኝ ወንጀል ፈፃሚዎች እና ወንጀሉ እንዲፈፀም ያመቻቹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች የሚሰሩ ሦስት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሦስት ደላሎች በአጠቃላይ 15 ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራው እየተካሔደ መሆኑ ተገጿል፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ የሙስና፣ ገቢዎችና ሸማቾች ወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ደርቤ ገቢሳ እንደገለጹት፥ ምርመራ እየተካሔደባቸው ከሚገኙት መካከል ሁለቱ ግለሰቦች በተመሳሳይ ስም አድራሻ በመጠቀም እና የፎቶግራፍ ለውጥ አድርገው እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ቤቶችን ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ተደርሶበታል፡፡

ግለሰቦቹ ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጣር ሀሰተኛ ሠነዱን በማዘጋጀት ዘጠኝ ባለሁለት፣ አንድ ባለ አንድ እና አንድ ባለ ሦስት መኝታ ቤቶችን በስማቸው ከወሰዱ በኋላ÷ ዘጠኙን ቤቶች ለሦስተኛ ወገን መሸጣቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ግለሰቦቹ በህገወጥ መንገድ ያገኟቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለሦስተኛ ወገን በብድር ዋስትና ማስያዣነት በመጠቀም በርካታ ገንዘብ ማጭበርበራቸውም ተረጋግጧል ብለዋል ኮማንደር ደርቤ፡፡

በዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳትፈዋል የተባሉ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ሕግ ፊት ለማቅረብ ክትትሉ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.