Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 6 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር መድረሱን ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት መጠን 6 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር ወይም 126 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ በግብርና ፣ ኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት እና ፋይናንስ ዘርፎች ዕድገት ማስመዝገቧን ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለፈው በጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ 6 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧን ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ ቀደም ሩዝ እስከ 5 ሚሊየን ኩንታል ከውጭ ሲገባ እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከሚመረተው ሩዝ 8 ሚሊየን ኩንታል እንደሚጠበቅ እና ከሀገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጪ መላክ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

ከ1 ሄክታር እስከ 70 እና 80 ኩንታል ሩዝ የተመረተባቸው አካባቢዎች እንዳሉና ይህም በቀጣይ ሩዝን ወደ ውጭ ለመላክ ተሥፋ ሰጪ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሩዝን እንደ ስንዴ ሁሉ በሥፋት ለማምረት የሚያነሳሳ ሁኔታ ተፈጥሯልም ነው ያሉት፡፡

በበጀት ዓመቱ ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ አዳዲስ የቡና ችግኞች መተከላቸው ተመላክቷል፡፡

በቀጣይም ከ20 በመቶ በላይ የምርት ዕድገት እንደሚጠበቅ ነው የተነሳው፡፡

የኢንዱስትሪው ዘርፍ 4 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ከግንባታ ዕቃዎች መወደድ እና ከአቅርቦት እጥረት አንጻር የዘርፉ ዕድገት ከ2014 በጀት ዓመት አንጻር መቀነሱንም ነው ያስረዱት።

የአገልግሎት ዘርፉ በ7 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን በማንሳትም ለዘርፉ ዕድገት የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ እና የኢትዮ-ቴሌኮም ሚና ከፍተኛ እንደነበር አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረውን ጫና ተቋቁሞ ትርፋማ መሆን የቻለ ተቋም ነውም ብለዋል፡፡

ኢትዮ-ቴሌኮምም ከ37 ሚሊየን በላይ የነበሩትን ደንበኞቹን ወደ 68 ነጥብ 9 ሚሊየን ማሳደግ እንደቻለም ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮ-ቴሌኮም በጀመራቸው አገልግሎቶች ገቢ ማሳደግ እንደተቻለና ዜጎች በቴክኖሎጂ ኑሯቸውን ማቅለል እንደቻሉም አንስተዋል፡፡

በሞባይል ባንኪንግም 25 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ከ134 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር መፈጸማቸውም ነው የጠቀሱት፡፡

ኢትዮ-ቴሌኮም በሞባይል የትራፊክ ቅጣት መክፈልን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሕይወት የሚያቀሉ አገልግሎቶች መሥጠት እንደቻለም ነው ያወሱት፡፡

የፋይናንሱ ዘርፍም በ21 በመቶ ማደጉ እና 2 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር መድረሱ ተጠቅሷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዜጎች ይቀርብ የነበረው የብድር መጠንም በ29 በመቶ ማደጉን አስረድተዋል።

በታምራት ቢሻው እና ዓለማየሁ ገረመው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.