Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር  8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ  ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ አደረጉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ የሚከተለውን መግለጫ አውጥተዋል።

የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋም

 

ሙስና ሀገርን የሚበላ ነቀዝ ነው፡፡ የሀገርን አንጡራ ሀብት እየቦረቦረ ጥሪቷን ባዶ ለማስቀረት ሌት ተቀን የሚማስን ተባይ ነው። ዋልጌ ባለሥልጣናት፣ በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎች እና ባለሃብቶች አንድ ላይ ሲገጥሙ፤ ከነዚህ የሌብነት ፊታውራሪዎች ጀርባ ብዛት ያላቸው ዜጎች መሰለፍ ሲጀምሩ ሙስና የተባለው ነቀዝ ሀገርን እንደ ወረርሽኝ ያጠቃታል፡፡ ሙስና በየትኛው ቦታና በየትኛውም ዘመን ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን የሀገርን ልማት አጥንቱ ድረስ እስከ መጋጥ ከደረሰ ሙስና አንድ አደገኛ ወረርሽኝ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ሙስና ሀገርን ሊያፈርስ የሚችል የደኅንነት ሥጋት መሆኑን ያስመሰከሩ ሀገሮችን በዘመናችን አይተናል፡፡ የአደንዛዥ ዕጽ፣ የኮንትሮባንድ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ንግድ፣ የንግድ ማጭበርበር ሙስናን ለዓላማቸው ማስፈጸሚያነት ይፈልጉታል፡፡ በዓለማችን የተጀመሩ ጦርነቶች እንዳይጠናቀቁ፤ ግጭቶች እንዳይበርዱ፣ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲጋጩ፣ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ ሙሰኞች ከዚህ አይነት ቀውሶች ስለሚያተርፉ ነው፡፡

 

ሙስና ዛሬ የሀገራችን የደኅንነት ሥጋት ሆኗል፡፡ ወደ ብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ እጅ ተወርች አሥሮ ለመያዝ ከጠላቶቻች እኩል ሙሰኛው እየታገለን ነው፡፡ የተስተካከለ ቢሮክራሲ፣ የተቀናጀ መዋቅርና ዘመናዊ አሠራር ለሙስና ተጋላጭነትን ስለሚቀንሱ፣ እነዚህን ለማጥፋት ወይም ለማሰናከል ሙሰኛው ቀን ከሌት እየሠራ ነው፡፡ሕዝባችን በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከመሬት ጋር በተያያዙ አሠራሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በሽያጭና ግዥ ሂደቶች፣ በፍትሕ አደባባዮች፣ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ የህዝብ ተቋማት ወዘተ. በሚያጋጥመው ሙስና እየተማረረ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ከጸጥታ ሥጋቶች እኩል ሙስና የብልጽግና ጉዟችን ዋናው ዕንቅፋት መሆኑን አንሥቷል፡፡

 

መንግሥት በየደረጃው የሚገኘውን መዋቅር በመፈተሽ፣ አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎችን እያሳለጠ ሥራዎችን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ በሙስና ወንጀል የሚሳተፉ አመራሮችንና ሌሎች ተዋንያንን ለሕግ በማቅረብ፣ ሙስና ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠርለት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ሀገራችን ያጋጠማትን ጦርነትና ኮሮናን የመሳሰሉ ወረርሽኞች የመንግሥትን ትኩረት ወስደዋል ብለው ያሰቡ ሙሰኞች፣ በየቦታው ተሠግሥገውና ኔት ወርክ ዘርግተው፣ ኢትዮጵያን ለማጥፋት እየሠሩ መሆናቸውን በዝርዝር የቀረበው የጥናት ሪፖርት ያሳያል፡፡ መንግሥት በጸጥታው ዘርፍ እንዳደረገው ሁሉ በሙስና ላይ ጠንካራና የማያዳግም ኦፕሬሽን ማድረግ እንዳለበት የጥናቱ ውጤትና የሕዝብ ውይይቱ ግምገማ ያመለክታል፡፡ በአንድ በኩል የመንግሥት ሕጎች፣ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሠራሮች ለሙስና ያላቸውን ተጋላጭነት የማጥፋት ሥራ ይሠራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሙስና ተዋንያንን የማጋለጥና በሕግ የመጠየቅ ተግባር ይከናወናል፡፡

 

መንግሥት በጥናት በደረሰባቸው የመንግሥት ሹመኞች፣ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች፣ አቀባባዮችና ጉቦ ሰጪዎች ላይ ምርመራ እያደረገ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ሙስና በባሕርዩ በረቀቀ መንገድ፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ አንዳንድ ጊዜም በሕጋዊነት ሽፋን የሚካሄድ በመሆኑ በመንግሥት ጥናት የተደረሰባቸው አካላትን ብቻ ለሕግ በማቅረብ የሚፈታ አይደለም፡፡ ሙስናን ከሥር ከመሠረቱ ለመንቀል እንዲቻል ከሕግና ከአሠራር ማሻሻያዎች በተጨማሪ፣ የሙስና ተዋንያን ሁሉ ሙስናን እርም እንዲሉ የሚያደርግ ርምጃ ያስፈልጋል፡፡መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡

 

ብሔራዊ ከሚቴው ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን፣ እነርሱም፡-

1. አቶ ተመስገን ጥሩነህ

2. ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ

3. አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ

4. አቶ ሰሎሞን ሶቃ

5. አቶ ደበሌ ቃበታ

6. ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ

7. አቶ አብዱሃሚድ መሃመድ ናቸው፡፡

 

ይህ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት እንዲችል የኅብረተሰቡ ሙሉ ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በሙስና ላይ በሚደረገው ዘመቻ ሊሳተፍ እንደሚገባ በተለያዩ መድረኮች ሲያነሣ ቆይቷል፡፡ መንግሥትም ይሄንን የሕዝብ ተሳትፎ በእጅጉ ይፈልገዋል፤ ምክንያቱም ሙስና በዋናነት የሚጠፋው ሕዝብ አምርሮ ሲታገለው ነውና፡፡

 

በመሆኑም ኅብረተሰቡ የሙስና ተዋንያንን በተመለከተ ያለውን መረጃ፣ ከቂምና ከበቀል ነጻ በሆነ መንገድ፣ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አድራሻዎች ለብሔራዊ ኮሚቴው በመላክ ሙስናን ለማጥፋት በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን፡፡ የሚቀርቡ ጥቆማዎች የጠቋሚዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ተገቢውን ጥንቃቄ እና ሚስጥራዊነት በጠበቀ መንገድ ተይዘው ይመረመራሉ። ብሄራዊ ኮሚቴው የሚወስዳቸው እርምጃዎች እና የእንቅስቃሴው ውጤት በየጊዜው ለህዝብ ይፋ ይደረጋል። የየክልሉ ርእሳነ መስተዳድሮች በየደረጃው የሚሠሩ ክልላዊ ኮሚቴዎችን በቅርቡ እንደሚያቋቁሙ በዚሁ አጋጣሚ እንገልጣለን።

 

▪ ስልክ ፡ 9555

▪ አጭር የፅሁፍ መልዕክት : 9555

▪ ድረ ገፅ ፡ http://www.9555pmo.et/

▪ ኢሜይል :  http://9555pmo.et/

▪ ቴሌግራም ፡ https://t.me/PMOfeedback

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.