Fana: At a Speed of Life!

ነገን ዛሬ ላይ ለመገንባት ባለ ጥረት እንደፋና ዓይነት ሚዲያ ያስፈልጋል- አቶ አብረሃም አለኸኝ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ነገን ዛሬ ላይ ለመገንባት ባለ ጥረት እንደፋና ዓይነት ሚዲያ እንደሚያስፈልግ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ አስተባባሪ ሚኒስትር አቶ አብረሃም አለኸኝ ገለፁ።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የአዳዲስ ፎርማቶች ማስተዋወቂያ፣ የገንቢ አስተያየቶች ማሰባሰቢያ እና 28ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማክበሪያ መድረክ ተካሄደ ።

በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደው መድረክ የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአድማጭ፣ ተመልካች እና ተከታዮች ተወካዮች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ አቶ አብረሃም አለኸኝ፥ ፋና በለውጥ ሂደት ላይ ለለውጥ የሚሰራ የሚዲያ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።

የሚዲያ ተቋሙ በስምንት የሀገር ውስጥ እና በሁለት የውጭ ቋንቋዎች በሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና ዲጂታል ሚዲያ  ይዘት በማድረስም ገንቢ ሚና እየተጫወተ ያለ ከጊዜ ጋር የሚራመድ ሚዲያ መሆናንም ነው የገለፁት።

መጪው ጊዜ ከመጣንበት ጊዜ በበለጠ ፈታኝ እንደሚሆን በመጠቆም ፈተናዎችን እንደዕድል  መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ የይዘት ዝግጅቱንና አቀራረቡን ሳቢ በማድረግም ከትናንት  በላቀ ሁኔታ ሚናውን ይጫወታል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

ህዝባዊነቱን በማጠናከር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ ሙስና እና የተደራጀ ስርቆትን በመዋጋት ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታልም ነው ያሉት።

የነበሩ መልካም እሴቶችን በማስፋት ኢትዮጵያን የሚሻግር ትውልድ የመገንባት ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ አብረሃም አሳስበዋል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮሮፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው፥ የሚዲያ ተቋሙ ላለፉት 28 ዓመታት በአካልም በመንፈስም ወደ ህብረተሰቡ ቀርቦ እየሰራ መምጣቱን አንስተዋል።

ፋና እስከዛሬ ከመጣበት መንገድ በላይ የተሻሻሉ፣ ወደ ህብረተሰቡ የበለጠ የሚያቀርቡ እና ነገን የተሻለ ለማድረግ የማያግዙ ይዘቶችንና አቀራረቦችን ይዞ መምጣቱን ይፋ አድርገዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተጀመረውን የሠላም ሂደት ያመጣውን መልካም እድል በመውሰድ የሀገሪቱን ከፍታ የማረጋገጥ ጥረትን የሚያግዙ  አዳዲስ ፎርማቶችን ፋና ይዞ መምጣቱን ነው የገለፁት።

እነዚህ ፎርማቶች ህብረ ብሄራዊነትን የሚያጎለብቱ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ  ሰው ተኮር መሆናቸውን አቶ አድማሱ ተናግረዋል።

በቀደመ ጊዜ ከፋና ጋር አብረው የነበሩ አድማጮች፣ ተመልካቾች፣ ደንበኞች እና መረጃ ሰጪዎች ለነበራቸው አጋርነት አመስግነው በማሻሻያ ትግበራ ሂደቱም አብረው እንዲዘልቁ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.