Fana: At a Speed of Life!

በእሲያ-ፓሲፊክ ሀገራት መካከል ነፃ ንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲተገበር ሺ ጂንፒንግ ጠየቁ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በታይላንድ እየተካሄደ በሚገኘው 29ኛው የእሲያ-ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር የመሪዎች ጉባዔ ላይ ነፃ እና ክፍት የንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ዕውን እንዲሆኑ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ጠየቁ፡፡

ሺ ጂንፒንግ ÷ “የዚህ መድረክ ዓላማ ማሌዢያ ላይ በፈረንጆቹ 2020 በተካሄደው ጉባዔ ላይ በፈረንጆቹ 2040 እናሳካለን ብለን ያስቀመጥነውን ርዕይ እና መርኅዎች ከወዲሁ ዕውን ለማድረግ በቁርጠኝነት ለመሥራት የምንነሳበት ነው” ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፍ እና ብዝኀነትን ያማከለ ብሎም ማንንም ያላገለለ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት ፣ የኢንዱስትሪ እና የአቅርቦት ሰንሰለቶች ትሥሥር ምኅዳርም ጥበቃ ሊደረግለት እና ደኅንነቱ ሊረጋገጥ እንደሚገባም ሺ ጂንፒንግ አሳስበዋል፡፡

ቻይና ገጠራማ አካባቢዎቿ ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች መሆኗም የተገለጸ ሲሆን፥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ይበልጥ ለማምረት ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎን ለማሳደግ እየሠራች መሆኑንም ሺ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የቻይናን የልማት ተሞክሮዎች እና የፈጠራ ሥራዎች በሁሉም የእሲያ-ፓሲፊክ ሀገራት በማሰራጨት የቀጠናውን ዘላቂ ልማት እና ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

በፈረንጆቹ ሕዳር 14 የተጀመረው እና ለተከታታይ 5 ቀናት ታይላንድ ላይ ሲካሄድ የቆየው 29ኛው የእሲያ-ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባዔ በዘላቂ የንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ መክሮ ዛሬ ይጠናቀቃል መባሉን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.