Fana: At a Speed of Life!

በከሚሴ ከተማ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከሚሴ ከተማ በክልል ደረጃ ተከብሯል፡፡

በዓሉ ”ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው፡፡

በበዓሉ አከባበር ላይ÷ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የኦሮሚያና የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች እንዲሁም የፌደራልና የክልል ከፍኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በበዓሉ አከባበር ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ኅብረብሔራዊነታችንን በዐደባባይ የምናሳይበት ነው ብለዋል፡፡

በአንድነቷ ያልፀናች ሀገር ብልጽግናዋን ማረጋገጥ አትችልም ያሉት አፈጉባዔው÷ አንድነትን ለማጽናት የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል መከበሩ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሐይማኖትና ዕሴት ባለቤት በመሆኗ በዓሉን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር የምናከብረው ያደርገዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባዔ ሀሊማ ይማም ባደረጉት ንግግር÷ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የቱባ ባህል ባለቤትና ብሔር ብሔረሰቦች በአብሮነት የሚኖሩበት ነው ብለዋል።

የበዓሉ መከበር የእርስበርስ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ ባህልና እሴትን ለማስቀጠል የጎላ ሚና አለው ተብሏል፡፡

በበዓሉ አከባበር የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ባህል፣ ወግና ልማድ የሚያሳይ የፎቶ ዐውደ ርዕይ ለዕይታ ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.