Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የሰላም ስምምነቱን መሰረት በማድረግ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እየተወጣ ነው – ዶ/ር ለገሰ ቱሉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት መሰረት በማድረግ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በተሟላ መልኩ እየተወጣ ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ አስታወቁ፡፡

አዎንታዊና ዘላቂ ሰላም የሚመነጨው ከውስጣዊ ፍላጎታችን ነው ያሉት ሚኒስትሩ ውስጣዊ ፍላጎታችን ወደ ውስጥ በመመልከት ቁስላችንን በማከም፣ የህዝቦች እኩል ተጠቃሚነትና አንድነት ማረጋገጥን ማዕከል የሚያደርግና ከእነዚህ ግቦች የሚመነጭ፣ ትልቁን ዓላማና የወደፊቱን ተስፋ የሚመለከት ከሆነ በእርግጥም ለአዎንታዊና ዘላቂ ሰላም መቆማችንን ያስረዳል ብለዋል፡፡

ለዚህም ሲባል ጥቃቅንና ለጊዜው ችግር የሚመስሉ፣ ከዘላቂ ጥቅም አኳያ ግን ፋይዳቸው እምብዛም ጉልህ ያልሆኑ ጉዳዮችን ለዋናው ግባችን ሲባል እንታገሳቸዋለን ብለዋል ሚኒስትሩ።

ነገሮችን ውጫዊ በማድረግ፣ ለጊዜው ከጥርጣሬና ፍርሃት የሚመነጩ ችግሮችን በማስተጋባት መጓዝ መቼም ቢሆን ብቻውን የመፍትሄ አካል መሆን እንደማይችል በመጥቀስም፥ ከዚህ አንጻር ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በዚሁ አግባብ መንግስት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት መሰረት በማድረግ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በተሟላ መልኩ እየተገበረ ነው ብለዋል፡፡

አቅም በፈቀደና አጋር አካላት ማቅረብ በቻሉት መጠን የሰብአዊ እርዳታና መድሃኒት በሁሉም አቅጣጫ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር በየሴክተሮቹ የሙያተኞች ቡድን ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለፁት ሚኒስትሩ፥ በአንደንድ አካባቢዎችም አገልግሎት መስጠትም መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በየደረጃው ያሉ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችም ሆኑ መገናኛ ብዙኃን በጥብቅ የሰላም ስምምነቱን መርሆዎች አክብረው እንዲንቀሳቀሱ እያደረገ መሆኑንም በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ገልፀዋል፡፡

ይህ የመንግስት ተጨባጭ ጥረትና ፍላጎት በሌላኛውም ወገን በስምምነቱ መርህ መሰረት ይበልጥ ወደ ተግባር መቀየር ይኖርበታልም ነው ያሉት፡፡

የሰላም ስምምነቱ መርሆዎች ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዳይቀየር እንቅፋት የሚፈጥሩ ሃይሎችንም ፊት ለፊት መታገል እንደሚገባ ጠቁመው፥ ለዘላቂና አዎንታዊ ሰላም የሁሉም ወገን ቅንነት የተሞላበት እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.