Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ከ7 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እና 364 ሜትሪክ ቶን መድኃኒት መሰራጨቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል 7 ሺህ 523 ሜትሪክ ቶን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች እንዲሁም 364 ሜትሪክ ቶን መድኃኒት መሰራጨቱን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል የሚገቡ የተለያዩ የሰብዓዊ እርዳታ እቅርቦቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አንስቷል፡፡

በዚህ መሰረት እስከ ሕዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም በ198 ተሽከርካሪ 6 ሺህ 93 ነጥብ 4 ሜትሪክ ቶን ምግብና አልሚ ምግብ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች መሰራጨቱ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባለፈም 364 ሜትሪክ ቶን መድሃኒት በክልሉ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች መሰራጨቱ ነው የተገለጸው፡፡

በተመሳሳይ 105 ሺህ 159 ሊትር ነዳጅ እና 1 ሺህ 74 ነጥብ 6 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች መሰራጨታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

የሰብዓዊ እርዳታውን በማሰራጨቱ ሒደት ከኮሚሽኑ ጋር 11 አጋር አካላት መሳተፋቸውም ነው የተገለጸው።

ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል የተጀመረው ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭትም በመንግስትም ሆነ በአጋር አካላት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.