Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረ መስቀል ጫላ በኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካን ሶንኪይ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም  በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከርና እና በቀጣይ በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት በሚያስችሉ  ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ÷  በሀገራት መካካከል ያለው የንግድ ግንኙነት እያደገ የመጣ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ አለመድረሱ በውይይቱ ተነስቷል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር  ገብረ መስቀል ጫላ ÷ ኢትዮጵያ ደቡብ ኮሪያ  የረጅም ጊዜ የንግድ  እና ኢኮኖሚ ትስስር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከደቡብ ኮሪያ ጋር ይበልጥ ለመስራት ፍላጎት ያለ መሆኑን ጠቁመው÷ ነባሩን የንግድ ስምምነት ገምግሞ ወደ ሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት ስምምነት ለማሳደግ የሚያስችል ሥራ መከወን አስፈላጊ መሆኑን  አስገንዝበዋል።

የንግድ ትስስሩን አጠናክሮ ለመቀጠል እንዲያግዝ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚንና የመንግስት ሙያተኞች አቅምን በመገንባት ፣  የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማመቻቸት፣ ተሞከሮንና ልምድን በማጋራት፣ የነጻ ገበያ አሰራርና የመደራደር አቅምን ለማሻሻል የአቅም ግንባታ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡

አምባሳደር ካን ሲንከይ በበኩላቸው÷ በቀጣይ ደቡብ የኮሪያ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ እንዲመቻችላቸውና ከሰፊው ገበያ ተጠቅመው ኢትዮጵያንም መጥቀም እንዲችሉ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት መፈራረም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ2030 የዓለም ኤክስፖን ለማዘጋጀት ሀገራቸው በውድድር ላይ መሆናን የገለጹት አምባሳደሩ÷ ውድድሩን ለማሸነፍ የኢትዮጵያ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.