Fana: At a Speed of Life!

ሙስና አሁን ካለው የኑሮ ውድነት በመቀጠል ከፍተኛ የሀገር ችግር ነው- ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሙስና አሁን ካለው የኑሮ ውድነት በመቀጠል ከፍተኛ የሀገር ችግር እንደሆነ በጥናት ማረጋገጡን የፌደራል የሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረው የጸረ ሙስና ስምምነት ቀን “ሙስናን መታገል በተግባር” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ሕዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ይከበራል፡፡

የፌደራል የሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ÷ ሙስና ድንበር ተሻጋሪ ችግር በመሆኑ ዓለም አቀፍ የጋራ ስምምነት መፈረሙን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያም ፈራሚ፣ አጽዳቂ እና ህጉን ተግባራዊ እያደረገች ያለች ሀገር ስትሆን÷ የሙስናን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ትግል ውስጥም የራሷን አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን አስረድተዋል።

የፌደራል የሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ባደረገው ጥናትም ሙስና በሀገሪቱ ካለው የኑሮ ውድነት ቀጥሎ የሀገር ችግር መሆኑን አረጋግጧል ነው ያሉት፡፡

ይህም የማህበራዊ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ጥያቄ ውስጥ በመክተት በመንግስትና በህዝብ መካከል አለመተማመንን እየፈጠረ ያለ አደገኛ ወንጀል መሆኑን አመላክተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የፀረ-ሙስና ድንጋጌ ጸድቆ ለፊርማ የቀረበበት በፈረንጆቹ ታህሳስ 9 ቀን ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሕዳር 30  ቀን ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን ይከበራል።

ኢትዮጵያም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንድ አካልና የድንጋጌው ፈራሚና አፅዳቂ እንደመሆኗ ቀኑን ለ18ኛ ጊዜ ታከብራለች ነው ያሉት።

የሙስና ተግባራት ሲፈጸሙ የሚመለከት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በ9555 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ በመስጠት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በይስማው አደራው እና ዙፋን ካሳሁን

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.