Fana: At a Speed of Life!

የተሻለች አፍሪካን ለመፍጠር ወጣቶች ላይ መሥራት እንደሚገባ አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካን መፃኢ ዕድል ብሩህ ለማድረግ እና የተሻለች አፍሪካን ለመፍጠር የአፍሪካ መሪዎች ወጣቶች ላይ ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

አቶ ደመቀ በኒጀር ኒያሚ ከተማ እየተካሔደ ከሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ ጉባዔ ጎን ለጎን በአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ የአህጉሪቷ ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክስ ግብይትና ሌሎች መሰል ውጥኖችም በአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት ሊደገፉ ይገባል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ግብይቱ የምርጥ ተሞክሮ ማሳያ ሊሆን እንደሚገባ  እና አፍሪካ በዓለም አቀፉ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ፍትሐዊ ድርሻዋን ማግኘት እንዳለባት ገልጸው÷ ይህ ካልሆነ ግን የአፍሪካ ሕዝቦች ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ሊያገኙ አይችሉም ብለዋል፡፡

የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ ለመፍታት እና አፍሪካውያን ጥበብን ለማሳደግ ብሎም ለመጠበቅ ተመሳሳይ የዲጂታል ተሞክሮዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ጉባዔ በፈረንጆቹ 2021 ያወጣው ሪፖርት እንዳመላከተው÷ ከ26 ነጥብ 3 ትሪሊየን ዶላር ዓለም አቀፍ የኢ-ኮሜርስ የግብይት ዋጋ መጠን ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ አንድ በመቶ ብቻ ነበር፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.