Fana: At a Speed of Life!

የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል ሁሉም አካላት በርብርብ ሊሰሩ ይገባል-ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የሚመለከታቸው ሁሉም አካላት በርብርብ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

“ሴቶችን አከብራለሁ ጥቃቷንም እከላከላለሁ” በሚል መሪ ቃል የ16 ቀናት ፀረ -ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ የመክፈቻ መርሐ ግብር በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንደገለፁት÷ የሴቶች ጥቃትን ለመከላከል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በርብር ሊሰሩ ይገባል፡፡

ለተጎጂዎች ማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው÷ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውም የጉልበትም ሆነ የስነ ልቦና ጥቃት ኋላ ቀር ድርጊት ነው ብለዋል።

የሴቶች ጥቃት ለመከላከል የክልሉ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ የተገኙ ውጤቶችን ዕውቅና በመስጠት በተሻለ ለመስራት መትጋት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስቆም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ችግሮችን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሆነ መግለጻቸውንም ከርዕሰ መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ ÷ በሴቶች ላይ የሚደርሱ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል በሚኒስቴሩ ከፍተኛ ስራ መሰራቱንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡

ጦርነት በተከሰተበት ወቅት በሴቶች ላይ የደረሰ ጥቃትን የማጣራት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.