Fana: At a Speed of Life!

እስካሁን ከ17 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የሰብዓዊ እርዳታ ምግብ ወደ ትግራይ ክልል ተልኳል -ተመድ 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ ካሳለፍነው ሕዳር 15 ቀን ጀምሮ እስካሁን 17 ሺህ 80 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና 699 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስ ወደ ትግራይ ክልል መላኩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ እንደገለጸው  ÷ የኢትዮጵያ መንግስት እና አጋር አካላት በትግራይ ክልል ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሚያደርጉት የሰብዓዊ እርዳታ የማዳረስ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በዚህ መሰረት በፈረንጆቹ ካሳለፍነው ሕዳር 15 ቀን 2022 ጀምሮ እስካሁን በ435 ተሽከርካሪዎች ከ17 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የእርዳታ ምግብ ወደ ትግራይ ክልል መላኩን አስታውሷል፡፡

በተጨማሪም 699 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎችን የጫኑ 19 ተሽከርካሪዎች እና 100 ሺህ 159 ሊትር ነዳጅ በክልሉ መሰራጨቱን አስታውቋል፡፡

ለሰብዓዊ እርዳታው ስራ ማስኬጃም 21 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ነው የተመላከተው፡፡

የሰብዓዊ እርዳታውን ለተጎጂ ወገኖች በማሰራጨት ረገድ 11 አጋር አካላት መሳተፋቸውንም ድርጅቱ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሪፖርትን ጠቅሶ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡

በቀጣይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በግጭቱ ሳቢያ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁማል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.