Fana: At a Speed of Life!

ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ በትብብር እንደምትሰራ ገለጸች

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የመረጃ ጄኔራል መኮንኖች በሠላም እና ፀጥታ ዙሪያ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡
በመድረኩም ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በሌሎች ዘርፎች ተባብረው እንደሚሰሩ ሁሉ በሰላምና ደህንነት ጉዳይም ተባብረው መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል፡፡
በኢፌዴሪ መከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ በኩል ሜጄር ጄኔራል ደምሰው አመኑ÷ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በሁሉም መሥክ በትብብር የመሥራት ታሪክ ያላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ወደፊትም ደህንነትን ለማሥጠበቅ በፀጥታ ዙሪያ በጋራ መሥራቱ አስፈላጊና ተመራጭ ነው ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ መረጃ ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል ማርሻል ስቴፈን ባባነን በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የሁለቱን ሀገራት ሰላም ለማረጋገጥ፣ የአካባቢ ደህንነትን በጋራ በጠበቀ አኳኃን እየሠሩ መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡
በቀጣይም በሠላም እና በፀጥታ ዙሪያ በቅንጅት እና በትብብር ይሠራሉ ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ህዝብ የቆዬ ታሪክ፣ ባህል እና ወግ ተጋሪዎች በመሆናቸው ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ የህዝቦች ተጠቃሚነት መቀየር አስፈላጊ መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል፡፡
ለዚህም ሰላምና ደህንነት ወሳኝ በመሆኑ የተጠናከረ የመረጃ ልውውጥ መኖር እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱ ነው የተገለጸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.