Fana: At a Speed of Life!

ልማት ባንክ ለግብርና ሜካናይዜሽን የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ለደንበኞች አስረከበ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከጀርመን ልማት ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለሊዝ ፋይናንስ ደንበኞቹ ያቀረባቸውን የሰብል ማጨጃና መውቂያ መሳሪያዎች አስረከበ።

በርክክቡ ስነ-ስርዓቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አስፋው አበራ እና በአዲስ አበባ የጀርመን ልማት ባንክ ዳይሬክተር ዲያና ሄድሪክ ተገኝተዋል።

አቶ አስፋው አበራ ÷ ጀርመን የኢትዮጵያ ግንባር ቀዳሚ የልማት አጋር መሆኗን ገልጸው÷ ለግብርና ሥራ ለሚያገለግሉ መሳሪያዎች ግዥ የሚውል ድጋፍ በማድረጓ አመስግነዋል።

ለባንኩ የሊዝ ፋይናንስ ደንበኞች የተላለፊት እያንዳንዱ መሳሪያ በቀን እስከ 1 ሺህ 200 ኩንታል ምርት የመውቃት አቅም ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የጀርመን ልማት ባንክ እንዲሁም በግብርና ሚኒስቴር የትብብር ማዕቀፍ በማዘጋጀት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም በሊዝ ፋይናንሲንግ የአሰራር ሥርዓት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በግብርና ሜካናይዜሽን ፕሮጀክት ከጀርመን ልማት ባንክ በተለቀቀ 13 ሚሊየን ዩሮ 33 ኮምባይነሮችና 9 ትራክተሮች ለደንበኞች መተላለፋቸውን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት ርክክብ የተደረገባቸው መሳሪያዎችም የዚሁ ፕሮጀክት አካል መሆናቸውን መሆናቸውንና በግዥ፣ በመመረትና በመጓጓዝ ላይ የሚገኙ መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ የጀርመን ልማት ባንክ ዳይሬክተር ዲያና ሄድሪክ በበኩላቸው ÷ መሳሪያዎቹ የግብርና ሥራን በማዘመንና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የያዘችውን ስትራቴጂ በመደገፍ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።

የጀርመን ልማት ባንከ በኢትዮጵያ በዘርፉ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ማረጋገታቸውንም የባንኩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.