Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል በቅርቡ ተፈናቅለው ከነበሩት 69 ሺህ ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ወደ ቀያቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል በቅርቡ ከተፈናቀሉ 69 ሺህ ሰዎች መካከል 34 ሺህዎቹ ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለሳቸውን የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራርና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታወቀ።

በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ማሒ ዓሊ፥ በሰው ሠራሽ ችግር ምክንያት ከበራሕሌ፣ አብዓላ፣ መጋሌ፣ ያሎ እና ጉሊና አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች÷ በጎራዒ፣ ሙሊ፣ በባራይራ፣ ሱዋን፣ ዶርታ እና ዲርማ የመጠለያ ጣቢያዎች ይኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ለተፈናቃዮቹም፥ ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶችን፣ የመንግሥት ተቋማትን፣ ሌሎች አደረጃጀቶችን እና የህብረተሰብ ክፍሎችን በማቀናጀት በአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል አማካኝነት ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በጎራዒ፣ ሱዋን፣ ዶርታ እና ሙሊ መጠለያ ጣቢያዎች የነበሩ 34 ሺህ ተፈናቃዮች ሙሉ በሙሉ ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለሳቸውን እና የውኃ፣ የትምሕርት እና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በበራይራ እና ዲርማ የመጠለያ ጣቢያዎች ደግሞ 35 ሺህ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁመው፥ ወደ መኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አቶ ማሒ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎቹ የሚገኙትን ተፈናቃዮች ከቀበሌ ቀበሌ የተፈናቀሉ እና ከወረዳቸው ያልወጡ በመሆናቸው ወደ ቀያቸው የመመለሱን ሥራ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም ረገድ ክፍተት መኖሩን ያነሱት አቶ ማሒ፥ ቀደም ሲል በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ልክ ምላሽ እያገኘ አለመሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ የማድረጉ ሥራ የሁሉንም ባለድርሻ አካላትና ረጂዎችን ድጋፍ እንደሚፈልግ ጠቅሰው ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.