Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ማዕድን ልማት ቢሮ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ለሚገነቡ 11 ባለሃብቶች የምርመራ ፈቃድ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ለሚገነቡ 11 ባለሃብቶች የምርመራ ፈቃድ መስጠቱን የአማራ ክልል ማዕድን ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ግንባታዎች ከመጓተት እስከ መቆም መድረሳቸው ተገልጿል፡፡

የክልሉ ማዕድን ልማት ቢሮ የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ ዳይሬክተር ብርሃኑ ታየ÷ በአማራ ክልል የሚስተዋለውን የሲሚንቶ እጥረት ለመቅረፍ የክልሉ ማዕድን ልማት ቢሮ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የምርመራ ፈቃድ የወሰዱ ባለሃብቶች ምርመራ ካከናወኑ በኋላ ወደ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ እንደሚገቡ ጠቁመው÷ እስካሁን ሁለት ባለሃብቶች ግንባታ መጀመራቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ 16 የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች መኖራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ÷ ከእነዚህ ውስጥ የክልሉ ድርሻ ከ 0 ነጥብ 5 በመቶ በታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ሲሚንቶን ለማምረት ሙሉ አቅሙን እንዲጠቀም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የግንባታ ፈቃድ መስጠት ብቻውን መፍትሔ ባለመሆኑ የመብራት ኀይል አቅርቦትና ሌሎች የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች ለሚገነቡት ፋብሪካዎች ሊሟሉላቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ማዕድን ልማት ቢሮ የሲሚንቶ ፋብሪካ ለሚገነቡ ባለሃብቶች ከታክስ ነፃ የሆኑ የፋብሪካ ማሽነሪዎችና ሌሎች ቁሳቁስ እንዲያስገቡ እንደሚያመቻችላቸው ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.