Fana: At a Speed of Life!

ህዝቡን ከፀጥታ ስጋት ለማላቀቅና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ ነው-ዶክተር አለሙ ስሜ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህዝቡን ከፀጥታ ስጋት ለማላቀቅና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን መንግስት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አለሙ ስሜ ገለፁ ።

ዶክተር አለሙ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ዶኒ ከተማና አካባቢዋ የሚገኙ ነዋሪዎች ጋር በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

ዶክተር አለሙ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት÷ ህዝቡ ልማቱን በተረጋጋ መልኩ ለማከናወን እንዲችል ሰላምን ማስፈን ቀዳሚ የመንግስት ትኩረት ነው ።

መንግሥት ለህዝብ የሚጠቅም አጀንዳ አለኝ የሚልና ይሄንንም በሰላማዊ መንገድ የሚያራምድ አካልን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው ጸጥታን በማወክ የሰላም ስጋት የሆነውን የሸኔን ጥቃት ማስቆምም ሌላው የመንግስት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ስንቅና መረጃ በማቅረብ ከጥፋት ቡድኑ ጋር የተሰለፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በህብረተሰቡና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ መረጃ ሰጪዎችን ጭምር የማጥራት ስራ በዘላቂነት ይሰራል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ።

በውይይቱ የተሳተፉ ነዋሪዎችም ፀረ ሰላም ሃይሎችን ለማስወገድ መንግስት የሚያደርገውን ህግ የማስከበር እርምጃ በሙሉ አቅማቸው እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.