Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አራት ወራት 22 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በአራት ወራት ውስጥ በመደበኛ እና የማዘጋጀ ቤት የገቢ ማሰባሰብ ስራ 22 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡

የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ÷በክልሉ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የኦሮሚያ ክልል በመደበኛ እና የማዘጋጀ ቤት የገቢ ማሰባስብ ስራ 22 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አንስተዋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ7 ነጥብ 4 ቢለየን ብር ብልጫ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ የክልሉ ህዝብ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች የገጠመውን ችግር ተቋቁሞ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በህዳር ወር 2014 ዓ.ም በድሬደዋ ከተማ የተረከበውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ዋንጫ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች እና ከተሞች በማዘዋወር በቦንድ ግዢ ፣ በስጦታ እና በ8100 A አጭር የሥልክ መልዕክት 1ቢለየን 35 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በ2014/15 የምርት ዘመን 6 ነጥብ5 ሚሊየን ሄክታር በዘር የተሸፈነ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው ÷ ከዚህ ውስጥም ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታሩን ለመሰብሰብ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

2 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታሩ ደግሞ በባህላዊ እና ዘመናዊ መንገድ በመታገዝ የምርት ብክለትን በመቀነስ ተሰብስቧል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ክልሉ ከ2014 ጀምሮ አቮካዶን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን የገለፁት ሃላፊው ÷በ2015 የምርት ዘመን 26 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መልማቱን ተናግረዋል፡፡
ሃላፊው በግብርናው መስክ በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ስራ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው÷ በ2015 ምርት ዘመን በሁለት ዙሮች 1ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማልማት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከተማሪዎች ምገባ ጋር በተያያዘ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች በክልሉ ተጠቃሚ መሆናቸው ነው ያመላከቱት፡፡

በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ማህበረሰቡን በማስተባበር 6 ሺህ የመጀመሪያ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ባለፉት አራት ወራት 4 ሺህ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል።

ከወቅታዊ የክልሉ የፀጥታ ጋር በተያያዘም ባለፉት ዓመታት የሽብር ቡድኑን ሸኔ እኩይ አላማ ባለመረዳት የሽብር ቡድኑን ለተቀላቀሉ ወጣቶች ተደጋጋሚ ጥሪ ሲደረግላቸው መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

አሁንም ለሰላም የተዘረጋው እጅ አለመታጠፉን እና በድጋሚ ጥሪ መቅረቡን ገልፀው÷ የሽብር ቡድን ለማጥፋት የክልሉ ግዴታ በመሆኑ የማህበረሰቡን ሰላም ለማረጋገጥ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.