Fana: At a Speed of Life!

ከሳዑዲ ዜጎችን ለመመለስ እየተደረገ ባለው ጥረት ዙሪያ ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ለመመለስ እየተደረገ ባለው ጥረት ዙሪያ ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢፌዴሪ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ እና በጅዳ የኢፌዲሪ ቆንስላ ጽ/ቤት ቆንስል ጄኔራል አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል በሳዑዲ ዓረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳይ መምሪያ ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዶ/ር መሐመድ አልሸመሪ ከተመራ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በቅርቡ ዳግም የተጀመረውንና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሳዑዲ ዓረቢያ የተለያዩ የማቆያ ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎችን የማስመለስ ዘመቻ የስራ ሂደት ላይ በትኩረት መክረዋል፡፡

በመድረኩ በፍ/ቤት ፍርድ ተፈርዶባቸው የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁና በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ዜጎች ወደ ሀገር መመለስ የሚችሉበትን ሁኔታ፣ በተለያየ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ገብተው መውጣት ያልቻሉ ዜጎች በልዩ ሁኔታ ከሳዑዲ መንግስት ይሁንታ አግኝተው ወደ እስር ቤት ሳይገቡ ወደ ሀገር መሄድ የሚችሉበት አግባብ ትኩረት እንዲሰጠው ተነስቷል።

የህገ ወጥ ፍልሰትን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረመው የሠራተኞች የስራ ስምሪት ስምምነት በተቻለ ፍጥነት ወደ ትግበራ መግባት በሚችልበት ሁኔታ ላይም ውይይት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ዶ/ር መሐመድ ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ለዘመናት የቆየውን የእምነት፣ የታሪክ እና የባህል መተሳሰርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ አውስተዋል፡፡

መንግስታቸው የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረውን ጦርነት ለመቋጨት የደረሰውን የሠላም ስምምነት እንደሚያደንቅ ገልጸዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ የማቆያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎቹን ወደ ሀገራቸው ለማስመለስ ለሚደርገው ዘመቻ ያላሰለሰ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።

በተለያየ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ገብተው መውጣት ያልቻሉ ኢትዮጵያውያን በልዩ ሁኔታ አሻራ ሰጥተው መውጣት እንዲችሉ ሙሉ ድጋፍ ለማድረግ መንግስታቸው ፈቃደኛ እንደሆነም አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.