Fana: At a Speed of Life!

አርሜኒያ በሰላምና በዴሞክራሲ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደምትሰራ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አርሜኒያ በቀጣይ በሰላም፣ በዴሞክራሲ እና በማህበራዊ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር አርተም አዝናውሪያን ገልጸዋል፡፡

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከአርሜኒያ የፓርላማ አባላት ጋር የሁለቱን ሀገራት ሕዝባዊ ወንድማማችነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር አርተም አዝናውሪያን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት የተወሰደውን የሰላም እርምጃ የሚደገፍ ተግባር መሆኑን ገልጸው ÷በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት በሰላም፣ በዴሞክራሲ እና በማህበራዊ ዘርፎች በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና አርሜኒያን የሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነት ለማጠናከር በቅንጅት እንደሚሰሩም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

የአርሜኒያ ፓርላማ አባልና የኢትዮ-አርሜኒያ ወዳጅነት ቡድን አሌክሲይ ሳንዲኮቭ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት 18ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ ጠንካራ እንደነበር እና አሁን ላይ የፓርላማ ግንኙነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ በበኩላቸው÷ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን የሀገራቱ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የወዳጅነት ቡድን እንደሚቋቋምና ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ለስደት የተዳረጉ በርካታ የአርሜኒያ ዜጎችን ተቀብላ ያኖረች ሀገር መሆኗ መገለጹንም ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.