Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ከ600 ሺህ ዶላር በላይ የሚገመቱ ተሽከርካሪና ትጥቆችን ለፌደራል ፖሊስ ድጋፍ አደረገች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና መንግስት ከ600 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚገመቱ ተሽከርካሪዎችንና ትጥቆችን ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በዚህም አምስት ኮሮላ ክሮስ ፓትሮል ተሽከርካሪዎች፣ ጥይት መከላከል የሚችል አንድ ተሽከርካሪ፣ የግንኙነት ማሻሻያ ስርዓት ዲጂታል የፎረንሲክ ላብራቶሪ መሣሪያዎችን እና ገንዘብን ጨምሮ በአጠቃላይ ግምታቸው ከ600 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ድጋፉን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዥየዋን ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል አስረክበዋል::

በዚህ ወቅት ጀነራል ደመላሽ ተቋሙ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲፋጠን፣ የንግዱ እንቅስቃሴ እንዲጎለብትና የኢንቨስትመንት ደህንነት እንዲሳለጥ ሚናው ከፍተኛ መሆኑንና ይህንን ተግባርና ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ በቴክኖሎጂ መደገፉ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል::

ወንጀልን ለመከላከልና ለመመርመር የሚያስችሉ፣ የትራንስፖርት ደህንነት ለማስጠበቅ የሚውሉ የደህንነት መሣሪያዎች፣ የፎረንሲክ ዲፓርትመንትን የሚያጠናክሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ረገድ በቻይና መንግስት እስከአሁን ለተደረጉ ድጋፎች ምስጋና አቅርበዋል::

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዥየዋን በበኩላቸው÷ የሁለቱን ሀገራት መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና የኢትዮጰያ ፌደራል ፖሊስ የጀመረውን ለውጥ ጉዞ የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል የቻይና መንግስት በቀጣይ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር የተመራው የልዑካን የቡድን አባላትም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እያደረገ ያለውን የቴክኖሎጂ ሽግግር መጎብኘታቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.