Fana: At a Speed of Life!

የአርብቶ አደር ስርዓተ-ምግብ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምስት ክልሎች በ6 ዓመት የሚተገበር የአርብቶ አደር ሥርዓተ ምግብ ማሻሻያ ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል ክልል ጅግጅጋ ከተማ ዛሬ ይፋ ተደርጓል።

በመርሐ ግብሩ ማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት ላይ የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ጀነራል ዳይሬክተር አብዱል ካማራ፣ ከፌዴራል እና ከክልሉ የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በግብርና ሚኒስቴር እና በአፍሪካ ልማት ባንክ  ቅንጅት የሚተገበረው ፕሮጀክቱ፥ በስድስት ዓመታት ውስጥ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ይፋ በተደረገው ፕሮጀክት ላይ የተገኙት አቶ ዑመር ሁሴን÷ የዚህ ፕሮጀክት ይፋ መሆን የአርብቶ አደሩን ህይወት የሚቀይርና የስርዓተ ምግብ አቅምን ለመገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

አብዱል ካማራ በበኩላቸውየህዝቡን አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ላይ የሚሰራው ተቋማቸው በዚህ ፕሮግራም የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ማሳደግ ፣ በአካባቢው ሰላም እና ደህንነትን ማስፈን፣ የሴቶችና ወጣቶችን አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ይህ ፕሮጀክት የአፍሪካ ቀንድ ለምግብ እና ለሥነ-ምግብ የመቋቋም አቅምን ማጎልበት የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ኑሮ ለማሻሻል ወደ ስራ መግባቱ ተጠቁሟል ።

ፕሮጀክቱ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል በዋነኛነት በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች የገበያ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ የተለያዩ ስራዎችን ይሰራል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የኢትዮጵያ መንግስት ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውም በሥነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

በምንተስኖት ሙሉጌታ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.