Fana: At a Speed of Life!

ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ የዲፌንድ ኢትዮጵያ አባላት ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ የዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩኬ ግብረ ሀይል አባላት አስታወቁ፡፡
 
የዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩኬ አባላት ሁለተኛ ዓመት የምስረታ በዓላቸውን በለንደን የኢፌዴሪ ኤምባሲ አክብረዋል፡፡
 
በዩናይትድ ኪንግደም የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ÷ ባለፉት 2 ዓመታት ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ የውጭ ሃይሎች ከፍተኛ ጫና ለመፍጠር ያደረጉትን የተቀናጀ ጥረት ለመቋቋም ‘ኢትዮጵያን እንታደግ ’በሚል ግብረ ሀይሉ መመስረቱን አስታውሰዋል፡፡
 
ግብረ ሀይሉ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ቤተሰቦችና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የበኩሉን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በነበረችበት ወቅት በዲፕሎማሲ፣ በሚዲያ ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂና በሎቢ ራሱን በማደራጀትና ከሌሎች የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር በመተባበር የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፎችን በመጥራት በዩናይትድ ኪንግደም አዎንታዊ ሚና መወጣቱም አውስተዋል፡፡
 
የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን አባላቱ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀው÷ ዘላቂ ሀገራዊ ጥቅሞችን ለማረጋገጥ የጀመሯቸውን የገጽታ ግንባታ፣ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እንዲሁም ለኢትዮጰያ ምርቶች ገበያ የማፈላለግ ስራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል፡፡
 
የዲፌንድ ኢትዮጵያ ዩኬ ግብረ ሀይል አስተባባሪ አቶ ዘላለም ተሰማ በበኩላቸው÷ የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ መሰረት የሚጥል ውሳኔ በመሆኑ አባላቱ ለስምምነቱ ተግባራዊነት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አስረድተዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ ችግር ውስጥም ሆና በርካታ የልማት ስራዎችን ስታከናውን እንደቆየች አስታውሰው÷ የሰላም ስምምነቱ እነዚህን የልማት ስራዎች ይበልጥ ለማከናወን እድል እንደሚሳጥ መናገራቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.